ለመከሩ ሰራተኞች
...የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት፡፡ ሉቃስ 10፡2
የእግዚአብሔር አሳብ
ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡
/ወይቤሎሙ፡ ሑሩ፡ ውስተኩሉ፡ ዓለም፡ ወሰብኩ፡ ወንጌል፡ ለኩሉ፡ ፍጥረት፡፡ / ማርቆስ 16፤15
ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ ትዕዛዝ የሰጠን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወንጌል መስበክ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፡፡ እኛ ወደ ጌታ እስከምንሔድ ወይም ጌታ በዳግም ምፅዓት እስኪመለስ ድረስ የምንከውነው ታላቅ የሆነ ሰዎችን የማዳን ተገግባር ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ይኸው ወንጌልን የማሰራጨት ተልዕኮ ለጥቂቶች ብቻ የተተወ ይመስላል፡፡ ሌሎቹ ምንም የማይመለከታቸው ነውን? አንዳንድ ጊዜም በዘመቻ ይጀመርና በዘመቻ ሲተውም ይታያል፡፡ በእኔ እምነት አንድ ቤተክርስቲያን ወንጌል መስበኩዋን ማቆም ያለባት በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ድነው ካበቁ እና የዓለም ፍጻሜ ደርሶ ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ወንጌልን መስበክ ማቆምና እንደፈለግን አጀንዳውን መቀያየር የምንችል አይመስለኝም ፡፡ ቤተክርስቲያንን የመሰረታት እና ራስ የሆነላት ጌታ እስኪመለስ ድረስ አድርጉ ብሎ ያዘዘውን ተልዕኮ መፈጸም ይኖርብናል፡፡ ተቁዋሙ የእርሱ ነውና፤ በቤቱ የእርሱ ትዕዛዝ ሊተገበር እንደሚገባ አስባለሁ ፡፡
መሰረታዊው ነገር ይህ ሆኖ ሳለ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን በግድ ፣በፍርሀትና በመጨነቅ እንዳንሰብክ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ እንዴት እንስበክ ?... ከውስጥ በሆነ ፍቅር! በጋለ ስሜት! ነፍሳት እንዲድኑ ባለ እውነተኛ ቅንዐት / passion /፡፡ በነገራችን ላይ ለወንጌል ብቻ ሳይሆን፡ ሰለ ሌላውም ስለምናደርገው ነገር አስቀድሞ ፍቅርና መነሳሳት ቢኖረን ጥሩ ነው፡፡ ቶዘር የሚባል አንድ መንፈሳዊ ሰው እንደተነናገረው '' አንድን ነገር ከመስራት በፊት ለዚያ ነገር ፍቅርና መነሳሳት ያሻል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትልቁ ነገር፡ ከሌሎች ነገሮች ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ የውስጥ መነሳሳት፣ ለነፍሳት የሚኖረን ፍቅር ፣ ተልዕኮና አገልግሎት ሁሉ የሚገኘው ወይም የሚገነባው ለክርስቶስ ኢየሱስ ባለን ጥልቅ ፍቅር ላይ ተመስርቶ ነው '' ብሎአል፡፡
ከውስጥ የሆነ ፍላጎት /passion/ እንዴት ይመጣል?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለምሳሌ የነህምያን ታሪክ ብንመለከት፡ ከጦቢያና ሰንበላጥ የመጣበትን ዛቻ ና ማስፈራሪያ ሳይበግረው ህዝቡን አስተባብሮ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ 52 ቀናት ሰርቶ የጨረሰ ታላቅ ባለ ራዕይ ነው፡፡ የትልቅ ነገር ባለ ራዕይና ባለ ገድል ከመሆኑ በፊት ግን፡ እስራኤላውያን፡ ተግዘው በሄዱበት በስደት ምድር - በባቢሎን ቤተመንግስት ውስጥ በጠጅ አሳላፊነት ሙያ ተቀጥሮ ኑሮውን ሲገፋ የነበረ ሰው ነው፡፡አንድ ቀን ግን አናኒ የሚባል ወንድሙ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ወሬ ይዞ መጣ፡፡ ያንን ወሬ ሌሎችም የእስራኤል ሰዎች ሳይሰሙ አይቀርም፡፡ ከሰማው ነገር ተነስቶ አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነ ግን አናይም፡፡ ነህምያ ግን የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስና ፣የአባቶቹ መቃብር ያለበት ከተማ በር መቃጠሉን ሲሰማ ልቡ ተነካ፤ አያሌ ቀን ተቀመምጦ አለቀሰ፡፡/ነህ.1፤3-4/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡ በሰማይ አምላክ ፊት እያዘነ ይጾምና ይጸልይ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ውስጡ ሲነካ ነው ፡ወደ ቀጣዩ እንቅስቃሴ የተራመደው፡፡ ከሞቀ ስራው አስፈቅዶ ወጥቶ የሄደው፤ ሌሎችን ሁሉ አስተባብሮ ቅጥሩን ሰርቶ የጨረሰው፡፡
ልክ እንደዚህ የሆነ ነገር ስንሰማ፣ ስንሰበክ፣ ስንማር ወይም ስናነብ፣ ቅዱስ ቅንዓት ውስጣችን ሊገባ ይችላል፡፡ የወንጌል ቅንዓትም ወይ በዚህ መልኩ አልያም በሌላ መንገድ ውስጣችን ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል 15 ላይ የምናገኘውና ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት ፤ከመቶዎቹ መካከል አንደኛው በግ ወደ በረሀ ኮበለለ፡፡ ወዲያውም ሰውዬው የነበሩትን ዘጠና ዘጠኙን በመተው የጠፋውን አንዱን ሊፈልግ እንደሄደ ይገልጻል፡፡ያሉትን ዘጠና ዘጠኙን ይባርክልኝ ብሎ እንደ መቀመጥ ፡እንዴት ስለ አንድ በግ ብሎ ፍለጋ ወጣ ? ብንል፤ መልሱ ሊሆን የሚችለው ስለ አንድ ግድ የሚያሰኝ ጥልቅ ፍቅር ገብቶበት ነው! በጉ ጠፍቶ መተኛት አይችልም፡፡ ቀጥሎም ነገሩን ከልቡ ሆኖ እንደሚያደርገው የሚያሳየን '' እስኪያገኘው ድረስ አጥብቆ መፈለጉ ነው፡፡'' ቁ.4 ፡፡ ካገኘው በሁዋላ ደግሞ፡ ደስታውን የገለጠበት መንገድ በተጨማሪ ልቡንና ቅንዐቱን ያሳየናል፡፡ በጫንቃው ተሸክሞ ወደ ቤት አምጥቶ፣ ጎረቤቶቹን ጠርቶ፣ ደስታውን ገለጸ ይላል፡፡ ካደረጉስ ማድረግ እንዲህ ነው፤ እስኪያገኙ ድረስ አጥብቆ መፈለግ !
ዛሬ በኛ ዘመን ስንት በግ ጠፍቶብን ነው የተቀመጥነው?
እ.ኤ.አ. ሚያዚያ ወር 2012 ላይ ስለ ዓለም ህዝብ ቁጥር አንድ አለም አቀፍ ሪፖርት ወጥቶ ነበር ፡፡ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ሰዐት የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ገደማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 750 ሚሊዮን ወይም 11% የሚሆነው ህዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሚያምን፣ 2.6 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ወይም 38% ገደማ የሚሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሰማ ነገር ግን ያልተቀበለ / ሌሎች አዳኞች አሉ ብለው የሚያምኑ/ ፣ የተቀረውና ሰፊው ህዝብ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ወይም 50% ገደማ የሚሆነው ምንም የወንጌል መልዕክት ያልሰማና የክርስቶስን አዳኝነት ያልተቀበለ ነው፡፡
ከነበሩት መቶ በጎች አንዱ ቢጠፋ አክንፎ ያስኬደው ፍቅር ተጽፎልን ከሶስት ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ጠፍቶ ምንም ሳይመስለን ተረጋግተን መቀመጣችን ምን ያህል አዚም ቢደረግብን ነው? ማን ነው ይህን ታላቅ ቅንዐት ከውስጣችን የዘረፈብን? እርግጥ ነው በዚህ የተቀደሰ ተግባር ላይ የተሰለፉ ተግዳሮቶች በርካታ ናቸው፡፡ ውስብስብም ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታ ተልዕኮውን በሰጠበት ጊዜ " አይዞአችሁ እኔ እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎናል '' ማቴ.28፤20፤
ነፍሳትን ከሲኦል የመታደግ አገልግሎት በእግዚአብሔር መንግስት ካሉት አገልግሎቶች ሁሉ ላቅ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ትልቅ ውጊያ ያለበት አገልግሎት ነው፡፡ በስጦታ ካልሆነ በቀር ብዙዎች በምርጫ ደረጃ ላይመርጡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ታላቅ የነፍስ እርካታ የሚገኘውም ፡ የነፍስ ማዳን ርብርቦሽ ውስጥ እንደሆነስ ያውቃሉ? ሰው ከሲኦል ሲያመልጥ ያለ እርካታ!
ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ና ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-
1- ማቴዎስ ወንጌል 7፤7-8 '' ለምኑ ይሰጣችሁአል፤ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኩዋኩ ይከፈትላችሁዋል፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኩዋካ ይከፈትለታል፡፡'' እንደሚል፤ ከልባችን እየፈለግን እንለምን፡፡ በሩን እስኪከፍትና እስኪሰጠን ድረስ ደጋግመን በሩን እንቆርቁር፡፡ በተስፋ ቃሉ መሰረት በሩን ይከፍትልናል፡፡ ሌሎችን የምናተርፍበት የወንጌል ቅንዐት ከብዙ ጥበብ ጋር ወደ ልባችን ይገባል፡፡
2- ሁለተኛው የያዕቆብ መልዕክት 1፤17 ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ይላል፡-'' በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው ፤መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡'' ለወንጌል የመቅናት ስጦታ በጎም ፍጹምም ነው፡፡ ይህን በረከት ከጌታ ልንቀበል እንደምንችል ቃሉ ያሳያል፡፡
ፀሎት፡- ጌታ ሆይ የወንጌልን ቅናት እንድትሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምንሀለሁ፡፡
አሁን ለኛ ቀን ነው ሌሊት?
'' ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ላደርግ ይገባኛል፡፡ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡'' ዮሐ.9፤4፡፡
በሰው ህይወት ውስጥ ቀንም ሌሊትም አለ፡፡ ይህ ሁሉን ሰው ሲያጋጥም የኖረ፣ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡የምንሰራበት ምቹ ጊዜና ሁኔታ ይሰጠናል ፤ደግሞ ሌላ ጊዜ መስራት ብንፈልግና ጊዜ ቢኖረን እንኩዋ የወደድነውን ማድረግ የማንችልበት ሌሊት ደግሞ ይመጣል፡፡የተመቻቸው ቀን ላይ ያልሰራ፣ያልተጋ ሰው የማይሰራበት ሌሊት ሲመጣበት ይቆጨዋል፡፡
ከወንጌል መስበክ አኩዋያ እነዚህን ሁለት ሁነቶች በምድራችን ላይ እንኩዋ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንዱ ወንጌልን በነጻነት መስበክና ማስተማር የማይቻልበት ጊዜ ነበር፡፡ ምናልባት ደግሞ አሁን በአንጻራዊ ሁኔታ ቤተክርስቲያን በድብብቆሽ ከምትሰበሰብበትና ከምትሰራበት ሁኔታ ወጥታ ወንጌልን በትልልቅ አዳራሾች ና በአደባባይ መስበክ ችላለች፡፡ ይህ ሲባል ግን መቼም ዘመን ቢሆን ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ከሚገጥሙ ትንሽም፣ ትልቅም ተግዳሮቶች ጋር ማለት ነው፡፡
ይሁንና ይህንን ነጻነት ተጠቅመን የማንሰብክበት፣ የማንመሰክርበት ከሆነ ነገ ደግሞ ሌሊት ሊመጣብን ይችላል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚከሰት አይታወቅም፤ የወንጌል ተቃዋሚዎች በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አይለው ተነስተዋል ጌታም ለጊዜው ስለ ፈቀደላቸው ይመስለኛል፡ አንዳንድ በጸሎት መከልከል የማንችላቸውን ድርጊቶች ሁሉ እያደረጉ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ነገ በእኛ አካባቢ ምን ሊከሰት ይችላል? ከህግ ፣ከዲሞክራሲ አንጻር የሰው መብት አትንካ ፣የራስህን አመለካከት ሰው ላይ መጫን አትችልም፤ የስብከት ፍቃድ፣ የአገልጋይነት ፍቃድ....ወዘተ የሚሉ ነገሮች ከአሁኑ በራችንን እያነኩዋኩ ነው፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ወንድሞችና በዚያም ያለች ቤተክርስቲያን ሌሊት ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡ እንደሚሰማው መስበክ ና መናገር አይቻልም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር ምናልባት በቅርብ ጊዜ ምቹ ቀን ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ሀዘናቸውም ይጽናናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሁንና እኛ ግን ከእንደነዚህ አይነት ሁኔታዎች መማር አለብን እላለሁ፡፡
ወንጌልን በራሳችን ዘመን ...!
" ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ካገለገለ በሁዋላ አንቀላፋ፡፡" ሥራ.13፤35
ዳዊት በተሰጠው በራሱ ዘመን እንዲሰራው የተቀመጠለትን ነገር አድርጎ ማለፉን ነው ቅዱስ ሉቃስ የዘገበልን፡፡አሁን እኛ በእኛ ዘመን እንድንሰራው የሚፈለግ ታላቅ የእግዚአብሔር ዓላማ፡ በዋነኛነት ምን ሊሆን ይችላል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በሚደረጉ ጥረቶች ብዙ ሰዎች የተለያየ በጎም የሚመስሉ፣ በጎም ያልሆኑ አመለካከቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፊት ለፊት የተቀመጠላቸውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ ችላ ብለው ሲመራመሩ ፡አላስፈላጊ ወደ ሆኑና ከእግዚአብሔር የልብ ትርታ ጋር ግንኙነት ወደሌላቸው ፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን፣ ከትህትና ይልቅ ትዕቢትን ፣ለሌላው ከማሰብ ይልቅ ለራስ ብቻ በሚያደላ አፍቅሮ ነዋይ እየተሳቡ ገብተው ሲለፉና ሲሰቃዩ ማየት የተለመደ ነገር ሆኑዋል፡፡ሁሉም ድርጊቶች የሚፈጸሙት በእግዚአብሔር የዘመኑ አሳብ ፣ ራዕይ ና ጥሪ ስም ነው፡፡ በተለይም ቤተክርስቲያን ዋና ነገሩዋን ስትስት ከማየት በላይ የሚያም ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር ግን በዚህ ዘመን ማድረግ የፈለገውን አሳቡን በግልጽ ተናግሩዋል '' በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ የፍቃዱን ሚስጥር አስታውቆናልና፡፡'' በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን በክርስቶስ ለመጠቀቅለል ነው'' ኤፌ.1፤10፡፡ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንዲሆንና ለእርሱም እንዲሆን ባለ የመለኮት አጀንዳ ውስጥ ተሳታፊ መሆን ምን ያህል ታላቅ ዕድል ነው?! ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ የምናደርግበት መንገዱ ደግሞ ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ለሰው የሞኝነት መንገድ የሚመስል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን አስቀድሞ የታሰበ ዘዴ ፣ጥበብ ፣ ብልሀት ነው፡፡ '' ....ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ፣ ካልሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ''----የተባለበት ሚስጥር፡፡
ቤተክርስቲያን ሆይ ንቂ !
ጾምና ጸሎት ይዘን በወንጌል ሳይሆን በተለያዩ ዘመነኛ ሃጢያቶች ና ሱሶች ቀስ በቀስ እየተወረሰ ያለውን ህብረተሰብና አካባቢ እንዲሰጠን መጸለይ ብንጀምርስ ? ክፉ በብዙ እየተጋ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያን በሰበብ አስባብ የጸሎት ቀናት ፣ሰዐታት እያስቀነሰ ፣የማለዳ ጸሎቶች ፣ አዳር ጸሎቶችን እያስተወ፡ ያለምንም ውጊያ እየሰራ ያለ ይመስላል፡፡ መሳሪያዎቹዋን ቀስ በቀስ የተዘረፈችዋ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዐት መንቃት ይጠበቅባታል፡፡ ሙሽራው ሊመጣ በደጅ ነው እያልን ሙሽሪት ተገቢውን ልብስ ሳታደርግ ፣ሳትዘጋጅ እንዴት ይሆናል?
ቤተክርስቲያን ትውልዱን እየተናጠቀች ካልጸለየች ሌላ የተጋ ይወስዳቸዋል፡፡ ዲያቢሎስ ለራሱ አጀንዳ እንደሚጸልይ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጠጥራችሁ ለመነ" ሉቃ.22፤31 ፡፡ የሰይጣን ልመና ትውልድን የማበጠር፣ የማድከምና የመበተን ሲሆን : ጌታ ግን ስለ ጴጥሮስ '' እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ '' ይላል፡፡ምንም እንኩዋ ጴጥሮስ በፈተናው ተሸንፎ ክዶ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ በንስሀ ተመልሱዋል፡፡ ለመመለሱ ምክንያት የነበረው ግን ጌታ ስለ እርሱ ስለ ማለደለት ነው፡፡/ቁ.32/
ቤተክርስቲያን ዕቅድ ያላወጣችበትን ህዝብ እና ስፍራ ጠላት እያቀደበት ነው ፡፡ ሰሞኑን አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ ድርጅት ምን እየደረገ እንደሆነ ለማንም ጆሮ ባዳ አይደለም፡፡ የደከሙ መንግስታትን እያሰሰ ይቆጣጠራል ፣ ይደራጃል፤ ለምሳሌ ጋዳፊ የወደቁበት ሊቢያ፣ ሳዳም ሁሴን የወደቁበት ኢራቅ፣ በብዙ ጦርነት የደቀቀችውን ሶሪያ....እንደ የመን ያሉ ሌሎችንም አገሮች፡፡ በትንሽ ተዋረድ ደግሞ ወንጌል ለመስበክ ያላሰብንባቸው አካባቢዎች ና ጠንካራ ጸሎት የማይደረግባቸው ልል ቦታዎች ልክ ጠንካራ መንግስት እንደሌለባቸው አገሮች ለክፉው ስራ የተጋለጡ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ምን ምን ያልነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች እንደ ወረርሽኝ የጫትና የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ማከፋፈያ እና መጠቀሚያ ሆነው ሲታዩ ፤የዝሙት ማስፋፊያ፣ የመጠጥ ንግድ ቤቶች ፣ዳንኪራ ቤቶች እንደ ሰደድ እሳት በየቦታው በፍጥነት ሲስፋፉ፡ ከሁዋላ ደጀን የሆናቸው ና ዕቅድ አውጪው ማን ነው? በዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን የት ነች? ለትውልዱ ምን እያሰበች ነው?
በዚህና በዚያ ተወጥሮ ያለውን ወጣት ትውልድ ከጠላት መንጋጋ ለማላቀቅ ተግቶ እየጸለየ ያለ ማን ነው? የትውልድ ሸክም ያለበት የዘመኑ የወንጌል ሰው ማን ነው? ቀድማ አይታ የተነሳች ፣ እንደ ሰራዊት እየጸለየች ያለች የዘመንዋ ቤተክርስቲያን የቱዋ ነች? ለሚከፈቱ አጥቢያዎች አጀንዳ ያላት፣ ለወንጌል በጀት ያላለቀባት፣ የጌታ ዋነኛ አሳብ የገባት አጥቢያ የት ናት? ሲመስለኝ ሰይጣን የቤት ስራ ሰጥቶን ፡እርሱ የራሱን ስራ እየሰራ ነው፡፡ አንገብጋቢና ዋና ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ እንድንፈጅ ፣ እርስ በርስ እንድንለያይ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ ፣ቤተክርስቲያን ከቤተክርስቲያን ፣መሪዎች ከመሪዎች እንዲራራቁና እንዳይግባቡ ተደርገናል፡፡ እንደ ጥንቱዋ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስለ ተሐድሶ ወይም ስለ ሪቫይቫል ሊያስቡ በሚገባበት ጊዜ ላይ '' የማርያም አይን ጥቁር ነው ቡናማ ?''፣ '' በአንድ መርፌ ላይ ስንት መላዕክት ይቆማሉ?''፣ '' ቅዱስ ቁርባን ውስጥ ዝንብ ብትገባ ዝንቡዋ ትቀደሳለች ወይስ ቁርባኑ ይረክሳል ? '' በሚሉ ጭቅጭቆች ተወጥረው፣ በሐሳብ ተለያይተው፡ ውድ ጊዜያቸውን እንዳቃጠሉ ፤ ሰይጣንም ኑፋቄዎችን በቤተክርስቲያን አሾልኮ ለማስገባት ዕድል እንዳገኘ፡ ዘንድሮም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ብናስተውል መልካም ነው፡፡
ሩቅ የመሰሉን ነውሮች ቤተክርስቲያን ደጅ ላይ፣ ብቻ አይደለም ምስባኩ ላይ ከወጡ ቆዩ፤ የጺዮንን በር የተዳፈሩ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች እየሆኑ ነው ፡፡ እኛስ እንደ ዳነ ሰው ፣ እንደ ቤተክርስቲያን ምን እያሰብን ነው?
በመጨረሻ፡- ቢቻል የቤተክርስቲያን መሪዎች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ተሰብስበው አዳዲስ የወንጌል ምስክርነት ዕቅድ ቢያወጡ ፣
-ጥቂት በእግዚአብሔር ፊት ጊዜ እንዲወስዱና እንዲሰሙት ቢሆን መልካም ነው፡፡
እግሬን አታጥብም
ዛሬ እንድንማር ልቤ ውስጥ የተቀመጠው መንፈሳዊ መርህ ጥቂት የሚባሉ ነገሮችን ባለማድረግ የሚቀርብን ታላላቅ ዕድሎችን ስለ ማወቅና በተቃራኒው ደግሞ ጥቂት መታዘዞችን በመፈጸም ትልልቅ ዕድሎችን ወደ ህይወታችን ማስለቀቅ እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳን ነው፡፡
"...ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም ጌታ ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው፤ኢየሱስም መልሶ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም በሁዋላ ግን ታስተውለዋለህ፡፡ጴጥሮስም አንተ የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥብም አለው፡፡ኢየሱስም ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት፡፡....."ዮሐ.13፣6-10.
ጴጥሮስ ልክ ከላይ እንደተገለጸው እግሬን አታጥበኝም አለ፡፡ነገሩ ከትህትና አንጻር የተደረገ ይመስላል፡፡ አንተ የእኛ መምህርና ጌታ ስትሆን እንዴት ዝቅ ብለህ የእኛን አገልጋዮችህን እግር ታጥባለህ? አይነት ነው፡፡ነገር ግን በቀላሉ ደግሞ ሊስተው የነበረ ዘላላማዊ ሀሳብ ሲታይ በጣም ከባድ ነበር፡፡በቀላሉ አታጥበኝም! በማለቱ ካላጠብኩህ ዕድል ከእኔ ጋር የለህም ተባለ፡፡
ልክ እንደዚሁ የሚመስሉ ትናንሽ ነገሮችን መታዘዝ ስለሚያቅተን ይሆን፤፤ ብዙ ትልልቅ ነገሮችን የምናጣው? አንዳንድ ጥቃቅን የሚመስሉ ድርጊቶችና መታዘዞች ውስጥ የእኛ ዘላለማዊ ጉዳይ ተሰውሮበት እንደሆን ማን ያውቃል?
በብሉይ ኪዳን ንዕማን የተባለውን ሶሪያዊ አለቃን ከለምጽ ለመፈወስ እርሱ በጠበቀው የፈውስ መንገድ ሳይሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ 7 ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንዲል ታዞ ነበር፡፡እርሱ ግን መታዘዝን እንቢ አለ፡፡በሁዋላም አብረውት የመጡት ሰዎች ለምነውት ነው ወርዶ የታጠበው፤በቀላል ሁኔታ ግን ፈውሱን አጥቶ ነበር፡፡ አንዳንድ ፈውሶች እንደዚህ ባሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ውስጥ በጥቂት መታዘዝ የሚመጣ ይሆናል፡፡ወይም በጥቂት አለመታዘዝ ፈውስ ይዘገያል፡፡
ሮክ ፌለር የሚባል የአለማችን ቁጥር አንድ ሐብታም የነበረ፤በአንድ ወቅት ከነበረበት ብርቱ የሆድ ህመም የተፈወሰው ፡ተስፋ ቆርጦ በቀሪው ዘመኑ ድሀ ህጻናትን በገንዘቡ በሚረዳበት ወቅት ነበር፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሊባርከን ሲል የሆነች ቀላል ፈተና ልትገጥመን ትችላለች፡፡ ለምሳሌ የኢዮብን ሐብት በእጥፍ ለመመለስ እግዚአብሄር የቻለው ኢዮብ በቃላት ስለ ወጉትና ስላደሙት የቀድሞ ወዳጆቹ መጸለይ በመቻሉ ነው፡፡ ልክ ታዞ ሲጸልይ እግዚአብሄር ምርኮውን በእጥፍ መለሰለት ይላል፡፡ኢዮብ 42፣10.
የአንዳንድ ሰዎች በረከት እንዲህ ባለ መንገድ ተይዞ ቢሆን እግዚአብሔር ሰዎችን ይቅር እስክንል ድረስ ምርኮአችንን ሊይዝ ይችላል፡፡ልክ ሰዎችን ስንፈታ ና ለበደሉን መጸለይ ስንጀምር ነገሮች ባልጠበቅነው ሁኔታ እየተከናወኑ ይመጣሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደዚያች መበለት ሴት ለእርሱዋና ለልጁዋ የቀረውን ዱቄት- "ጋግረሽ በዘይት ለውሰሽ አምጪ" እንደማለት ያለ ትዕዛዝ ልንታዘዝ እንችላለን፡፡ አሁን በእውነት ይህች መበለት የሚወሰድባት ነች ወይስ የሚሰጣት? በመለኮታዊው ስሌት ግን የረሀቡን ዘመን በጥጋብ ለማለፍ ያላትን መስጠት ነበረባት ፡፡ ያንንም ታዛ አደረገች እግዚአብሔርም ባረካት፡፡
ስለዚህ አንዳንድ የማይጋጠሙ የሚመስሉ ትዕዛዞችን ብንፈጽም፣ ብንሸነፍ ፤ወይም ቶሎ ይቅር ብንል?....እግዚአብሄር ካዘገጋጀልን የተለያዩ ዕድሎች መጉደል አይሆንም፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በዘላለማዊው ጸጋው ይርዳን ማስተዋልንም ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
በርዕሳችን መሰረት ጴጥሮስ እግሬን አልታጠብም ቢልም ቅሉ፤ ነገሩ የእርሱን ከጌታ ጋር የመሆንና ያለመሆን ዕድል ፈንታ የሚያስወስን መሆኑን ሲረዳ ጌታ ሆይ እግሬን ብቻ አይደለም ሰውነቴን ሁሉ እጠበኝ አስብሎታል፡፡ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን አሜን፡፡
ሰጥቶም ነስቶም ሲያየን?!
ብዙ ጊዜ በህይወታችን የምናልፋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡አንደኛው ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው ማጣት ይሆናል ፡፡ይህ ምናልባት ገንዘብ ነክ በሆነ ጉዳይ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡አንዳንድ ጊዜ ደስ የሚሉ ቀኖች በህይወታችን ይከሰታሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ መኖርንና መፈጠርን እስኪያስጠላ ድረስ ሊኮን ይችላል፡፡ደግነቱ የመከራና የችግር ዘላለማዊ ማህተም ማንም ላይ ስላልታተመ፤ ደግሞ ከደረሰብን ጉዳትና ከገጠሙን ችግሮች በጸጋው አገግመን ሌላ ደስታና ሰላም ውስጥ ስለምንገባ እግዚአብሔር ይመስገን ፡፡
ለዛሬው ርዕሳችን የኢዮብን ህይወት በመጠኑ ብንዳስስ አሰብኩ፡-ኢዮብ ትልቅ የሚባል መከራ ውስጥ የነበረ ጻድቅ ሰው ነበር ፡፡ ለምን ያን ሁሉ መከራ ደረሰበት ? የነበረውን ያን ሁሉ ሐብት እንዴት በአንድ ጊዜ አጣ ? የሚስቱ መኮብለል፡የልጆቹ መሞት፣የወዳጆቹን ማጣት፣ከዚህ ሁሉ ጋር የእርሱ በቁስል መመታት ...ለኢዮብ ምን ያህል አስከፊ ወቅት እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡ይህ ሁሉ ለምን እንደ ደረሰበት ኢዮብ በጊዜው የገባው ነገር ባይኖርም ለእኛ ለአንባቢዎች ግን የተገለጠ ነገር አለ፡፡ቃሉ እንደዚህ ይላል፡-
‹‹....እግዚአብሄርም ሰይጣንን በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትከውን? እንደሱ ፍጹምና ቅን እግዚአብሄርን የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲ ብሎ መለሰለት በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን ? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን?.... ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ በእውነት በፊትህ ይሰድብሀል፡፡እግዚአብሔርም ሰይጣንን እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው፡፡›› ኢዮብ 1፤6-12
ከላይ እንደተገለጸው ሰይጣን የኢዮብን መስግድ፣የሰርክ መስዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ና ማምለኩን፤ ከበዛለት ጥበቃና ከተደረገለት አንጻር ብቻ እንደሆነ ነው እያስረዳ የነበረው፡፡ ነገሩ እንካ በእንካ አይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የኢዮብ መሰጠትና አምልኮ ከሁኔታዎች ጋር የተያያዘ አይደለም አለ፡፡በኢዮብ ላይም ከነበረው ጽኑ መተማመን አንጻር ሲሆንለት፣ ሲበዛለት ያመልካል፡፡ ከነጠከው ና ከነሳኸው ግን በፊትህ ይሰድብሀል፡ ተብሎ እየተከሰሰ ያለውን ሰው ሒድና አረጋግጥ፣ ያለውን ሁሉ ጉዳበት፡ እርሱን ግን ተው ብሎ ፈቀደለት፡፡
ጌታ እንዲህ ሊተማመንብን ይችል ይሆን? ብዙ የተደረገላቸው እና አላቸው የሚባሉ ሰዎች ቢነሳቸው በቤቱ ይቀጥላሉ ወይ? በተቃራኒው ምንም የለሌላቸው ሰዎች ሲሆንላቸውና ሲሳካላቸው የድሮውን ፍርሀትና አምልኮ ይቀጥላሉ ወይ? ከችግር፣ ድህነታቸው ከተላቀቁ በሁዋላ ጸባያቸው የተቀየረ የድሮውን እግዚአብሔርን መፍራታቸውን ትተው፣የሰርክ፤የማለዳ ጸሎታቸውን ትተው በመዝናናት የተኩ ስንት ናቸው? የሰጣቸው ነገር ከሰጪው ያራቃቸው ስንት ናቸው? ከቤተ ክርስቲያን ፣ከተለያዩ መንፈሳዊ ህብረቶች እርቀው ያሉ ስንት ናቸው?
እግዚብሔር ግን ስለ ኢዮብ በድፍረት ተናገረ፡፡ ባይኖረውም ያመልከኛል፡፡የእርሱ ከእኔ ጋር መሆን ነገሮች አይደሉም ምክንያቱ ...እርሱ እኔን እንጂ ያለኝን ብቻ ፈላጊ አየይደለም! እንደማለት ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ኢዮብ ተፈትኖ ያለፈ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ሚስቱ እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ብላ ከተናገረችው በሁዋላ ኢዮብ ከመለሰው ክፍል እንኩዋ ብናይ ኢዮብን በቀለላሉ መረዳት ይቻላል፡‹‹..በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም፡፡›› ም.2፤9-10 :: ኖሮት በድሎት ያመለከውን ጌታ አጥቶ ነጥቶም እርሱ ጻድቅ ነው ብሎ መስክሩአል፡፡ እግዚአብሄርም ስለ እርሱ የተናገረው ለሶስቱ ሰዎች "እንደ ባሪያዬ ኢዮብ ስለ እኔ ቅንን ነገር አልተናገራችሁም" ኢዮብ 42፤8--፡፡
ምናልባት በቅዱሳን ህይወት የተለያዩ ፈተናዎች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ለምሳሌ የሚወዱዋችሁ ሰዎች ቢጠሉዋችሁ፣ በቤተሰብ አካባቢ ያልታሰበ ነገር ቢገጥማችሁ፣ በዙሪያችሁ ያሉ ደስ የሚሉ ነገሮች ድንገት ቢቀየሩ፣ የተማመናችሁበትን ስራ ብትለቁ፣ምናልባት ኑሮ እንደ በፊቱ ባይሆንላችሁ፣ ብርቱ ወዳጆቻችሁ / ያመናችሁት ሰው / ቢከዳችሁ፣ነገሮች እንደምትፈልጉት ሳይሆኑ ሲቀሩ....ወዘተ እንደ ድሮአችሁ አምልኮአችሁን ትቀጥላላችሁ ወይ ? ነው ፈተናው፡፡
ከድህነትና ባለጠግነት ጋር በተያያዘ ጠቢቡ ሰለሞን የተናገረው አንድ ነገር አለ ‹‹ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ: እንዳልጠግብ እንዳልክድህም እግዚአብሔር ማን ነው? እንዳልል ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል. ›› /ምሳ 30፤8-9/ ከቃሉ አንጻር የድሀ ፈተናው ከማጣቱ የተነሳ በእግዚአብሄር ስም ሀሰት እንዳይናገር ሲሆን ፤ የባለጠግነት የጎንዮሽ ችግር ደግሞ: እግዚአብሔር ማን ነው? የማለት፤ ‹ገነንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ.› እስካለኝ ድረስ ማንም ምንም ሊያደርገኝ አይችልም!! የሚል አጉል ትዕቢት ውስጥ መግባት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ልከኛ የሆነ ኑሮን ለራሱ የተመኘው፡፡ለነገሩ በሁለቱም ጎን /ሳይዶች/ ችግሮቹ እየታዩ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ ድሆች ለምን አፍሪካዊ ሆንን? ለምን ጠቆርን? ለምን ይሄ ና ይሄ የለንም ? የሚሉ ጥያቄዎችን አንግበው የክህደት አቅጣጫ ሲይዙ:: ባለጠጋዎቹ ደግሞ ሌሎችን በመናቅ፣ለራሳቸው የተለየ ስፍራን በመስጠት ተነጥለው ይኖራሉ፡፡
ሰዎች የተለያየ በረከት ሲሰጣቸው እና ስኬት ውስጥ ሲገቡ ሊያስቡዋቸው የሚገቡ ጥቂት ቁም ነገሮች አሉ፡፡ምናልባትም ለክፉ ነገር እንዳንነሳሳ እንደ ማርከሻ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ከዚያም በችግር ወቅት ምን ማሰብ እንዳለብን ጥቂት እናያለን፡፡
1- ትናንትናን/መነሻችንን/ አለመርሳት
‹‹ዛሬ አንተን የማዘውን ትዕዛዙንና ፍርዱን ስርዓቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤ከበላህና ከጠገብክ በሁዋላ ፣መልካምም ቤት ሰርተህ ከተቀመጥክ በሁዋላ ፣የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በሁዋላ .፣ ብርህና ወርቅህ ያለህም ከበዛልህ በሁዋላ ፣ልብህ እንዳይጉዋደድ.....አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ በልብህም ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል፡፡›› ዘዳግም 8፤11-18
2- የተሰጠኝ ነገር በጎ ስራ እንድሰራበት ነው በሚል ዕቅዶችን ማውጣትና ሌሎችን በመርዳት ጉዳይ መንቀሳቀስ
‹‹ በአሁን ዘመን ባለጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በህያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው ፡፡እውነተኛውን ህይወት ይይዙ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሰረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ስራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው፡፡ ›› 1ጢሞ.6፤17-19
ብዙዎች በአሁን ጊዜ ከረሀብና ከጥጋብ የትኛው ያስቸግራል ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡አንዳንዶች እንደ ዳዊት በችግር /በስደት/ ዘመን ታማኝ ሆነው ኖረው ፤ሲነግሱ ሲያልፍላቸው የሚበድሉ አሉ፡፡ዳዊት ከነገሰ በሁዋላ ነው አስከፊ በደሎችን የሰራው ፤በሰራዊቱ ልቡ የታበየው፤ የታማኝ ወታደሩን የኦርዮንን ሚስት የደፈረው፡፡ሌሎች ደግሞ በችግር ወቅት የጣሉት ብዙ መንፈሳዊ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ኤሳው ውድ የሆነ ብኩርናውን ለሚጠፋ መብል የለወጠው በራበው ጊዜ ነው፡፡
3- በጊዜውም አለጊዜውም መጽናት.........ቃሉ በህይወት የሚገጥሙ ሁለቱን ገጽታዎችን ነው የሚጠቁመን፡፡በጊዜው የሚለው የሚመችና ደስ የሚለውን ቀናት ሲሆን፤ያለ ጊዜው የሚለውz ደግሞ ደስ አይሉም የምንላቸውን የማይመቹ ክፉ ቀናትን ነው፡፡
ምናልባት በዚህ ጊዜ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ያላችሁ ይህ ዘመን አልፎ ሌላ የበረከት ሁኔታ ውስጥ ትገባላችሁ ብዬ በጌታ ታምኜ እነግራችሁዋለሁ፤ ነገር ግን ሁሌም የማይለወጥና ያው የሆነ ህይወት እስከመጨረሻ እንድንይዝ አስቀድመን ልንጸልይ ይገባል፡፡በተደላደለ ሁኔታ ያላችሁም ሰዎች ምንም ማድረግ የማትችሉበት ክፉ ቀን ሲመጣባችሁ ታማኝነታችሁ ሳይጎድል ጌታን መጠበቅ እንድትችሉ ተግቶ መጸለይ ያሻል፡፡
በመጨረሻ ሰጥቶም ነስቶም ቢያየን ያው አምላኩን የሚፈራና የሚያመልክ አውነተኛ ክርስቲያን ሆነን አንዲያገኘን ጌታ በዘላለማዊ ጸጋው ይርዳን በማለት በሮሜ 8 ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ወስጄ ትምህርቴን አጠቃልላለሁ ፤ጳውሎስ እንደጠቀሰው ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል ? ይልና ሁለቱን ዓይነት ገጽታዎች ያስቀምጣል ፡፡ በተለይ " ከፍታም -ዝቅታም" የሚለው ቃል ውስጤን ይስበዋል፡፡ በህይወታችን በተለያየ መንገድ ከፍታ ሲመጣም ፣ ደግሞ ዝቅታዎች ሲገጥሙን ዘላለማዊው ፍቅሩ ያለመናወጥ ውስጣችን ይደር አሜን፡፡.
አስተያየት ና ጥያቄ ደግሞ የጸሎት ርዕስ ካለዎት በአድራሻው ይጻፉ፡፡ benjabef@gmail.com
ንገስባት!
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ሐጢያት በርካታ ቦታዎች ላይ ተጠቅሱአል፡፡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በብርታትም ፣በድካምም አልፈዋል፡፡ ሁሉም ነገር ለትምህርታችን የተጻፈ ነው፡፡ ዛሬ በዚህ ርዕስ ስር የተወሰኑትን በማንሳት በሐጢያት ላይ መንገስ መጽሐፍ እንዴት እንደሚያስተምረን እናያለን፡፡
ሐጢያት ምንድን ነው?
1- የመጀመሪያው ሐጢያት ያለመታዘዝ ነው፡፡ ዘፍ .3፤11
2- ሐጢያት ቶሎ የሚከብ ነገር ነው፡፡ ዕብ.12፤2
3- በደጅ /በልብ/ የሚያደባ ነገር ነው፡፡ ዘፍ.4፤7
4- ዕድል ካገኘ በስጋ ላይ መንገስ የሚችል ነው፡፡ሮሜ 8፤12
ሐጢያትን ልክ እንደ ኮምፒውተር ቫይረስ ውሰዱትና፤ ቫይረስ እንዴት በስርዐት የተቀመጡትን ፕሮግራሞች እንደሚያዛባ፤መረጃዎችን እንዴት እንደሚያጠፋ፤እንዲሁም የተለመደውን ስራ እንዳይሰራ እንዴት እንደሚያስተጉዋጉል መመልከት ይቻላል፡፡ሐጢያትም ልክ እንደዚሁ በሰው ውስጥ ያሉትን በጎ ራዕይና ዓላማዎች እንዳይሳኩ የሚያደናቅፍ ፣ ሰውን ከአምላኩ የሚለይ፣ከራሱ የተፈጥሮ ሁኔታ አስወጥቶ ሌላ ፍጡር የሚያስመስል፤ እንዲሁም ሰዎች ለሰዎች ካላቸው የተቀደሰ ህብረትና ግንኙነት የሚለይና የማበላሸት አቅምን የሚጨምር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ክርስቶስን ከዙፋን አስወርዶ ወደ ምድር ያመጣውን፣ ታላቅም የህይወት ዋጋን ያስከፈለው ሐጢያት እንደቀላል በማየት በህይወታቸው ዕቃቃ የሚጫወቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ለኀጢያት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጥ ክርስቲያን ኀጢያት ምን እንዳስከፈለ በትክክል አልተረዳም እንደ ማለት ነው፡፡
ቫይረስ በአንቲ ቫይረስ እንዲጠፋ እንዲሁ የሐጢያት ማስወገጃው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደሙ ነው፡፡ምክንያቱም የፈሰሰው በትክክል ለሐጢያታችን ማስተሰርያ በመሆኑ ነው፡፡ምናልባት አንቲ ቫይረሶች እንደየ ሁኔታው ሊለያዩ ቢችሉም፡ አንዳንድ ጊዜ አንዱ አንዱን ማጥፋት ላይችል ይችላል፡፡ ዓለም ላይ ለተሰራው ማንኛውም ሐጢያት በሙሉ ግን መንጻት የሚቻለው በክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ለሐጢያት ሌላ ተስተካካይ ክፍያ የለውም ወይም የትኛውም ሀይማኖታዊ ና በጎ ተግባራት ለበደል መቀነሻነት /ማስተሰረያነት/ ሊውሉ አይችሉም፡፡ይህ የክርስቶስን ደም ማቃለል ነው የሚሆነው፡፡
ታዲያ በሀጢያት ላይ መንገስ የምንችለው እንዴት ነው?
ከዚህ በፊት እሰቲ የሐጢያት ምንጩ ከየት እንደሆነ እንመልከት......ማርቆስ ወንጌል ም.7 ቁ.20 እስከ 23 ላይ ሲናገር እንዲህ ይላል " ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው፡፡ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ ሐሳብ፣ዝሙት፣ መስረቅ፣መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው፤ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፡ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡" በዚህ መሰረት ሐጢያት ከውጪ የሚመጣ ነገር ሳይሆን ከውስጥ ያለ ግፊት ነው ማለት ነው፡፡ ልክ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ከመስረቁ ወይም ዝሙትን ከመፈጸሙ በፊት ልቡ ውስጥ ያስባል፡፡ዝሙትና ስርቆቱ ድርጊቶቹ እና ፍጻሜዎቹ ናቸው፤ እንጂ ቀድሞም ቢሆን በልብ ፣በሐሳብ ሳይጨረስ ወደ ድርጊት አይገባም፡፡አንድ ሰው ሰኞ ላይ ሆኖ ቅዳሜ ስለሚፈጽመው ሐጢያት ሊያስብ ይችላል፡፡ ሐጠጢየያተቱ ሰኘኞ ጀምሮአል እንጂ ገና ቅዳሜ አይደለም የሚጀምረው፡፡አሁን ርብርቦሹ የተደረጉ ሐጢያቶች ላይ ሆኑዋል፡፡ ነገር ግን ጥራትና ጽዳት የሚያስፈልገው ምቹ ቀናትና ሁኔታን እየጠበቀ ያለ ውስጣዊ ሐጢያት ላይ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ታዲያ የሰይጣን ተሳትፎው ምንድን ነው? ካልን ክፉ ሐሳብ መላክ፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት..ወዘተ ነው ፡፡እንጂ የማንንም እጅ ይዞ ና ጠምዝዞ ሐጢያት አያሰራም፡፡ ሔዋንንም ቢሆን በቃልና በሐሳብ ነው የማረካት ድርጊቱን ያደረገችው እርስዋ ነች፡፡
ለሰው ልጆች ሁሉ ውድቀት ሰበብ የሆነው የህይዋን ስህተት የመጣው ሰይጣን ሐሳቡዋን አበላሽቶት ነው፡፡ 2ቆሮ.11፤3 ፡፡ ሐሳቡ የተበለላሸበት ሰው ወደ ድርጊቱ ለመግባት ቀላል ይሆንለታል፤ ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የዳዊት ልጅ አቤሴሎምም ወንድሙን አምኖንን ከመግደሉ በፊት ረጅምና የቆየ የግድያ ሐሳብ አርግዞ ነበር፡፡ ጊዜውና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ደግሞ አስገደለው፡፡ 2ሳሙ.13፤2፡፡
አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሐሳብ ያድርና ድርጊቱ ሊቆይ ይችላል፤ ይህን ጊዜ መንቃት ነው፡፡ ምንም እስካላደረኩ ድረስ ንጹህ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ቀን የሚጠብቅ ክፉ ምኞት ላይ መንገስ ያስፈልጋል፡፤ እግዚአብሔር ቃኤልን ቀድሞ ያስጠነቀቀው ለዚያ ነው፡፡ ደጅህ ላይ ሐጢያት እያደባች ነው ንገስባት አለው፡፡ አለዚያ እርሱዋ ትነግስብሃለች፡፡ ያን ጊዜ ፍቃዱዋን ታደርጋለች፡፡እግዚአብሄር ወደ ቃየን መጥቶ ከነገረው ነገር የምንማረው ኀጢያት ላይ እኛ መንገስ ካልቻልን ኀጢያት በእኛ ላይ መንገስ ይጀምራል፡/ ዘፍ.4፤7/የሚለውን ነው፡፡
ያዕቆብ 1፤15 ላይ ሲናገር '' ምኞት ጸንሳ ሐጢያትን ትወልዳለች ፡ሐጢያትም ጸንሳ ሞትን ትወልዳለች፡፡ " ሞት የሚባለው /ውድቀት ሊሆን ይችላል/፤ ከመከሰቱ በፊት ውስጥን ይዞ የሚከርመው ሐሳብ /ምኞት/ ነው፡፡ ምኞት ዝም ከተባለ ቆይቶ ቆይቶ ሀጢያትን ይወልዳል፡፤ ከዚያም ወደ ሞት ያመጣል፤ ሁሉም ሂደት ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያትን፣ሞትንና ውድቀትን በህይወቱ ማየት የማይፈልግ ሰው ራሱን ማንጻት ያለበት ከውስጥ ነው፡፡ ምን አርግዣለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንዲሰጥ በቅድሚያ ሐሳብ ነው የመጣበት፡፡ '' ዲያቢሎስም ሐሳብ ካስገባ በሁአላ ''ይላል፡ ምናልባት ዲያቢሎስ ወደ አዕምሮው የላከበትን ሐሳብ መቃወም ይችል ነበር ፡፡ ምናልባትም ወደ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ሐሳብ ቀርቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም እነርሱ ተቃውመውት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ግን ሐሳቡን አስተናገደ፤ ወደ ቀጣዩ ና ከባዱ ነገርም አለፈ፡፡ ሮሜ 6፤12 ''...ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ሐጢያት አይንገስ '' ስጋችን ላይ ሐጢያት ሲነግስ እንደ ስጋ ፈቃድ ለመኖር የስጋን ነገር አዘውትረን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ /ሮሜ.8፤5/
ውስጡ የተሸነፈን ሰው ወደተገዛለት ነገር በቀላሉ መጎተት ይቻላል፡፡ ብዙ የሚያቅተው ከነገሮች ውስጥ መውጣት ሳይሆን ነገሮችን ከውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግራቸው ከግብጽ ውስጥ ወጥተው ነበር፡ ነገር ግን በቆይታ እንደታየው ግብጽ ውስጣቸው ነበረ፡፡ ስለዚህም በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ ይለናል፡፡/ሥራ.7፤39/፡፡ ከዓለም ወጥተን ግን ዓለም ውስጣችን ካለች እየዘመርን ፣ እየጸለይን ፣ ቤተክርስቲያን እየሄድን የሐጢያት ተጠቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ከሁሉ ነገር ተገልለው አንድፊቱኑ ገዳም ለገቡ መነኮሳት እንኩዋ ትልቁ ትግል የውሰጥ ነው፡፡ ከግብጽ ወጥተህ ግብጽ ግን ከልብህ ካልወጣ ችግር ነው፡፡የሎጥ ሚስት ከሶዶም በእግሩዋ ወጥታለች ነገር ግን ሶዶም ከውስጥዋ አልወጣም ነበርና እንቅፋት ሆነባት፡፡ መቀየር ፣መለወጥ ከውስጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በአዕምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ......" የሚለን፡፡ ከየ ዕለቱ ኑሮአችን እንኩዋ ብንመለከት አንድ ሰው ወተት ወይም ጎመን የሚጠላ ቢሆን፡ ከፈለገ ቦታ ቢመጣም ወይም ነጻም ቢሆን አይነካውም፡፡ ሐጢያትን ከውስጥ ስንጠላ አዩኝ አላዩኝ ከሚል መሳቀቅ እንወጣለን፡፡ በዚህም ላይ ውስጣችንን ቦርቡሮ በጊዜ ሒደት ከሚጥለን ነገር እንገላገላለን፡፡ ልክ እንደ ጎመኑ ና ወተቱ የትም ብንሆን ፣መቼም ቢሆን አንነካውም፡፡
አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ውስጡ ችግር ያለበት ሰው ያማረ ህንጻ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ቢገባ ችግሩ አያቆምም ብሎአል፡፡ የገባበት ቦታ ነገሩን ሊለውጥ ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ በጣም ወፍራምና ዕድሜ ጠገብ ዋርካ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን በሆነ ወቅት እምብዛም ነፋስ ባልነበረበት ጊዜ ነው ሌሊት ላይ ወድቆ የተገኘው ፤በጊዜው ሁኔታው ሲጠና ዛፉ በከፍተኛ ሁኔታ ውስጡ በብል ተቦርቡሮ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቅርፊት ተሸፍኖ ያለ እየመሰለ ኖረ፤ነገር ግን ባልታሰበ ቀን ወድቆ ተገኘ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደዚያ ይመስሉኛል ተሸፍነን ጠንካራ ሰዎች እንመስላለን፣ አስተማማኝ እና የመላዕክት ህይወት ያላቸው እንመስላለን፤ ምናልባት ውስጣችን ግን በብዙ እየተገዘገዘ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በየ አደባባዩ ላይ የሚሰሙት ውድቀቶቻችንም የዚህ ውጤት ይሆናል፡፡እስቲ ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ ና ነጻ እንውጣ ፡፡ ውድቀትን ብዙ ሰው ሊያየው ፣ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ያለን የውስጥ መቦርቦርና ትናንሽ ልምምዶች ግን እምብዛም አይታይም፡፡እኛው ከጌታ ጋር እንፍታው፡፡ልምምዱ ከፍ ያለ ደረጃ እንኩዋ የደረሰ ቢሆን በጾም ጸሎት በፊቱ ብንሆን የማይለወጥ ነገር ምንም የለም፡፡ ጌታ ሁሉን ይችላልና፡፡
ውስጣችን ያለውን፣ የምንቸገርበትን ነገር በምን እንደምናውቅና ፣ የውስጥን ትግል እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል በክፍል ሁለት ትምህርታችን እንቀጥላለን፡፡
ማስታወሻ:- ይህን ትምህርት ቅዱሳን እንዲጠቀሙበት ያድርጉ፡፡
በክፉ ቀን..!
'' ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ አንሱ፡፡'' ኤፌ.6፤10-19
የክፉው ቀን የቱ ነው? የክፉው ቀን መቼስ ነው?
ልክ እንደ አሁኑ ጊዜ ማለት ነው ፡፡ ብዙ ፈተና የበዘዛበት፣ የጸለዩት የማይሰማበት የሚመስልበት ቀን፤ ለጠላት የተፈቀደለት ቀን ይመስላል፡፡ ምናልባትም የዓለም ፍጻሜ ቀን የመጨረሻዎቹ ደቂቀ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህም ምጡ በዛ፣ እጅግ ዘግናኝና አሰቀቃቂ ነገሮች እየተከናወኑ ነው፡፡ ማስቆም አልተቻለም፣ ደግሞስ የቱን ከየትኛው ማስጣል ይቻላል? ብዙዎች በየቤታቸው እንቆቅልሽ ውስጥ ናቸው ያሉት፣ የፈተናው ና የመከራው ዓይነት ብዙ ነው፡፡ በፍጹም ያልጠበቅነው ነገር ገጥሞናል፡፡ በዚህ ከፉ ቀን የብዙዎች አቅም የሚፈተሸበት ፣ ጉልበታቸው የሚላላበት.፣ እምነታቸውን የሚፈትን ነገር የሚገጥምበት .....ጊዜ ነው፡፡
በሕይወት ያልታሰበ ነገር ሲገጥም ያስደነግጣል፤ ቢሆንም የመጨረሻው ዘመን ባህሪ በመሆኑ ልንታገስ ደግሞ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ እንደጻፈለት '' ነገር ግን በመጨረሻ ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና ፣ገንዘብን የሚወዱ ፣ትምክህተኞች ፣ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው ፣ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ ፣ሐሜተኞች ፣ራሳቸውን የማይገዙ ፣ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ ፣ከዳተኞች ፤ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፣ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኀይሉን ግን ክደዋል ከእነዚህ ደግሞ ራቅ፡፡" 2ጢሞ.3፤1-5
ማናችሁም ሰዎች የሆነባችሁ ነገር ከዚ ውጪ አይሆንም ብዬ እገምታለሁ፤ የሚያስጨንቀውን ዘመን ሁላችንም እየቀመስነው ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው መጽናት ብቻ ነው፡፡
አንዳንዱ ነገር ለምን እንደሆነብን እና እንደሚሆን ላይገባን ይችላል፡፡ አንገታቸውን በሰይፍ የሚቀሉ ሰዎች ብዛት፣ በህክምና ስህተት ያሳደጉዋቸውን ወላጆች የሚያጡ ሰዎች ብዛት፣ ጽኑ ወዳጅነት ወደ ጠላትነት መቀየር፣ ልጆችን በተለያየ አደጋ ማጣት፣ ክፉ ዘዴኛነት ፣ ብልጠት፣ ራስ ወዳድነት፣ ማታለል አስገራሚ ጭካኔዎች ሲሆኑ፤ ለምን ? እንዴት ማለታችን አልቀረም፡፡ ጌታ የት ሄዶ ነው ይህ ሁሉ የሚሆንብን ትሉ ይሆናል፡፡
የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ነብይ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበረ '' የምትመጣው መሲህ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ ?'' ብሎ ወደ ኢየሱስ መልዕክተኞችን ላከ፡፡ወንጀል ሳይሰራ እስር ቤት መግባቱ ፣ በዚህም ላይ ብዙ የመሰከረለት ብርቱው ኢየሱስ በርሱ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ፣ አልያም አንዳች ተዐምራት ሰርቶ እርሱን ከእስር አለማስፈታቱ አደናግሮት ይሆናል፤ ነገር ግን ከዚህም የከፋ ሆነ፡፡ በእስራቱ ጊዜ ዝም ማለቱ ሲገርመን ፡ ጭራሽ በሔሮደስ ልደት ላይ ለዘፈነች አንዲት ወጣት ብላቴና ጥያቄ መሰረት አንገቱ ተቆርጦ በወጪት ቀረበ፡፡ ጌታስ ? ዝም! በቃ ዝም!
አንዳንዱ ጉዳይ ከእኛ አዕምሮ በላይ ነው፡፡ ምናልባት ከጌታ ጋር መግባባት ስለማንችል ይሆን ዝም የሚለን? እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ሁሉን የሚችለው ጌታ በዙፋኑ ላይ ቆሞ እያየው ነበር፤ ለምን እንዳላስጣለው አይታወቅም፣ የታመነው ምስክሩ አንቲጳስ ሲገደል ጌታ ጣልቃ አልገባም ፣ ሐዋርያቱ በዘይት ተጠብሰው ሲሞቱ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት አናብስት ቦጫጭቀው ሲገድሉዋቸው የጠራቸው ጌታ በዙፋኑ ላይ ነበር፡፡ ለአንዳንዱ ጥያቄ መልስ በእጃችን የለም፡፡ አንድ የእግዚአብሔር ሰው እንዳሉት በፊሊፒንስ የጭቃ ጎርፍ 250 ህጻናትን ለምን ከድኖ እንደገደለ አናውቅም፡፡ በቅርብ ጊዜ አንድ የምታሳሳ ወጣት ከሲያትል ለሚሽን ጉዞ ወደ ህንድ ሄዳ በተመሳሳይ ለአገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ የሄደው መጋቢ አባት ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ተጠርቶ የመጣው ፡ ልጅህ ድንገት ሞታለች ተብሎ ተረድቶ ነበር፡፡ በጣም አሳዛኝ ነበረ፡፡ በሌላ ጊዜ አንድ ዘማሪት እህት እናቱዋን በሞት ያጣችው ኦፕራሲዎን ልታስደርጋቸው ወስዳ በወቅቱ ሐኪሞቹ መቀስና ሌሎች ነገሮች ሆዳቸው ውስጥ ረስተው ስለ ሰፉአቸው ነበር፡ ነገሩ ኢንፌክሽን ፈጥሮባቸው ዳግመኛ ሲደረጉ እንደሞቱ ነው ለቅሶ ስደርስ የነገረችኝ፤
ወገኖች ለእኛ የሚበጀን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው ፤ ጥያቄያችን ባይመለስም እናመልከዋለን ፣እንወደዋለን፡፡ እንደዚህ የመሰሉ ቀናትን ልናሸንፍ / ልንቁዋቁዋም / እንችላለን ፤የምንችለው ግን ፡ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር በመልበስ / በማንሳት/ ነው፡፡ መሳሪያው ሰው ሰራሽ ወይም አሜሪካ ፣ጃፓን ሰራሽ መሳሪያ ሳይሆን የእግዚአብሔር ዕቃ ጦር ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ክፉ ጊዜ እንዲሆነን ያዘጋጀልን መከላከያ እና ማሸነፊያ ዕቃ ጦር ነው፡፡ ቢያንስ ስድስት ነገሮች ናቸው ፤ቀጥለን እናያቸዋለን፡-
1- የእምነት መታጠቂያ- ወገባችን ላይ
2- የጽድቅ ጥሩር- ደረታችን አካባቢ
3- የሰላም ወንጌል- እግሮቻችን ላይ
4- የእምነት ጋሻ- በአንደኛው እጃችና ላይ
5- የመዳን ራስ ቁር- በጭንቅላታችን ላይ የሚደረግ
6- የመንፈስ ሰይፍ /የእግዚአብሔር ቃል ነው/- በቀኝ እጃችን ይዘን የምናጠቃበት ነው፡፡
ከ ራስ እስከ እግራችን ድረስ መሸፈን ያስፈለገን ምክንያት ጠላት እኛን ለመጉዳት ወይም ለመግደል ከጭንቅላታችን ጀምሮ ወርውሮ ስለሚሞክረን ነው፡፡ መዳኑ አስተማማኝ የሆነን ክርስቲያን ጭንቅላቱን መትቶ ሊጎዳው አይችልም፡፡ ነገር ግን ደረቱን በጥሩር ካልታጠቀ ማለትም ጽድቅ ላይ ገና የሚያመቻምች ሆኖ ካገኘው ይጎዳዋል፡፡ ነገር ግን እርሱም ከተሸፈነበት ቢያንስ እግሩን ስበሩት ብሎ መልዕክተኛ ይልካል:: ይህን ጊዜ ጠንካራ የወንጌል ከስክስ ያላደረገ ሆኖ ከተገኘ ፡ ባይሞትም እንኩዋ ዘመኑን ሁሉ በመንፈስ እያነከሰ ይኖራል ስለዚህ ሙሉውን ትጥቅ መታጠቅና መመላለስ አለብን፡፡ እንደሚታወቀው ሰይጣን ትንሽ ቀዳዳ ፈልጎ ነው የሚያጠቃን ፤ያልተሸፈነ አካላችንን ፈትሸን እንልበስ /እንታጠቅ/፡፡
የእስራኤል ንጉስ አክዐብ የሞተው በጥሩርና በጥሩር መጋጠሚያ በኩል ከጠላት ወገን በተወረወረ ቀስት ተወግቶ ነው፡፡ ምናልባት ሁሉን ታጥቆ ነበር፤ ይሁንና መቀነት ግን አላደረገም እንደማለት ነው፡፡ ምንም እንኩዋ በእርሱ ሞት ላይ ፍርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ የወጣም ቢሆን፡፡ጥቃት የደረሰበትና ለሞት የበቃው ግን በተገኘው ክፍተት በኩል ነበር፡፡
ወገኖች ሙሉ የእግዚአብሔርን ትጥቅ ታጥቀን በዚህ ዘመን እንድንኖር አሳስባችሁዋለሁ! እስቲ የላሉትን ጠበቅ እናድርጋቸው፤ ከትናንሽ ጥያቄዎቻችን እንውጣና ኩርፊያውን ትተን በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ ፣ በእውነት እንመላለስ!! የሚመጣልን መድኀኒት እርሱም ክርስቶስ ወደ ልዩ እረፍት ቦታ ይወስደናል፡፡ ብንጸና እንወርሳለን፡፡ በነገር ሁሉ ጌታ ከሁላችን ጋር ይሁን ፡፡ አሜን!!!
ማስታወሻ፡- ይህ ለቅዱሳን የተዘገጋጀ መልዕክት ነው፡፡
ቀን ሳለ
. የእድሜህ ዘመን ስንት ነው ?
. የሚሰራበት ቀንና ስለ ማይሰራበት ሌሊት አውቀዋልን?
የመግቢያ ጥቅሶች
''....ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ልፈጽም ይገባኛል፡፡ ማንም የማይሰራባት ሌሊት ትመጣለችና፡፡'' ዮሐ.9፤4
''.....አንተ እንድሰራው የሰጠኸኝን ስራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ ፡፡'' ዮሐ.17፤4
እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የሚያስረዱት የመጀመሪያው የተሰጠንን ተልዕኮ እና ዓላማ በተሰጠን ቀን ቶሎ ልንፈጽመው እንደሚገባ እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ አልፎ ማንም ሊሰራባት የማይችልባት ሌሊት እንደምትመጣ ነው፡፡ ከተፈጥሮ እንደምንረዳው ቀን የሚባልና ሌሊት የሚባሉ ጊዜዎች አሉ፡፡መንፈሳዊውም ልክ እንደዚሁ ነው፤ ከተፈጠርንበት ዓላማ ጋር የምንሰራበት ጊዜም አብሮ ይሰጣል፡፡ እርሱን በዋዛ፣ በፈዛዛ ካሳለፍነው ደግሞ ቢመኙም እንኩዋ ከብዙ ነገር አንጻር ምንም ማድረግ የማይቻልበት ጊዜ ይመጣል፡፡
ቀኖቻችን የተመቻቹ አጋጣሚዎቻችን ናቸው፡፡ጤናችን አፍላ ጉልበታችን፣ የተትረፈረፈ ሰዓታችን ሊሆን ይችላል፡፡ብዙ ነገሮችን በቀላል መንገድ መስራት የሚያስችሉን የዘመነኛው ቴክኖሎጂዎችም በተወሰነ መልኩ መልካም አጋጣሚዎቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ፡፡ ምናልባት አንዳንድ ህጎች፣ፖሊሲዎች...ወዘተ ቀን እንደሆነልን ሊጠቁመሙን ይችላሉ፡፡ ምናልባት ዛሬ ክፍት የሆኑ ነገሮች ነገ ላይዘጉ ፤ ዛሬ እንደልብ ልናገኛቸው የምንችላቸው ነገሮች ነገ ላይወደዱ የሚችሉበት ምንም መተማመኛ ነገር የለም፡፡ የተትረፈረፈ ጊዜያችን ነገ ላይ በጭንቅም ላይገኝ ይችላል፡፡መጠቀም ዛሬን ነው፡፡ የምንችለውን ሁሉ አድርጎ ማለፍ !
ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሰጠው ጊዜ ጨርሶ በሰማይ ወደ ነበረው ክብር እንደሚመለስ ያለውን ነገር ነው የሚያስረዳው፡፡ ተልዕኮን በአንድ በተሰጠ ጊዜ ጨርሶ ፈጸምኩ ማለት እንዴት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው ?! ጳውሎስም ይህንኑ ነው ያለው .....ሩጫውን ጨርሼአለሁ ...........!
በሰው ህይወት ሁሉ የምንሰራበት ቀን እና የማንሰራባት ሌሊት አለች፡፡አሁን ቀን የሆነላችሁ ፡ ማለትም ከብዙ ነገር አንጻር ነገሮችን ለማድረግ ዕድሉ የተመቻቸላችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ የይለፍ አረንጉዋዴ መብራት የበራላችሁን......የሚወክል ሲሆን፤ለሌሎች ደግሞ ሌሊት ውስጥ ያላችሁ ትኖራላችሁ ፡፡ ማለትም ምንም ነገር ለማድረግ ነገሮች ያልተመቻቸላችሁ፣ ማድረግ ብትፈልጉም ማድረግ ያልቻላችሁ፣ የጊዜ እጥረት ያለባችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ ቀይ መብራት ስለበራ ማለፍ የማትችሉትን ጭምር ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ቀን ለሆነላችሁ በአግባቡ ጊዜውን እንድትጠቀሙበት ፣ ሌሊት የሆነባችሁ ደግሞ ተመልሶ በቸርነቱ ቀን እስኪያመጣላችሁ በጸሎት በመትጋትና በእምነት ጠንክራችሁ እንድትጠብቁ እመክራለሁ፡፡
ጊዜ ማለት ውድ ነገር ነው፡፡ የሚቆምበት እግር ያልተፈጠረለት ወፍ እንደማለት ነው ፡፡ ልናቆመውና እንዲጠብቀን ልናደርገው አንችልም፡፡ ለምሳሌ የትናንትናው ቀን ተመልሶ ሊመጣ ይችላልን ? አይችልም፡፡ ልክ ከአፋችን እንደወጣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ /የተቃጠለ አየር/ ነው፡፡ ያስወጣነውን አየር መልሰን ልናስገባ አንችልም፡፡ ተቃጥለው ያለፉ ጊዜዎችም ልክ እንደዚህ ናቸው ፤ በነበራቸው ጊዜ አንዳች ሳይሰሩበት ከርመው በባነኑ ሰዐት ማጣፊያው ያጠራቸውና የቆጫቸው አያሌ ናቸው፡፡ የሌሊቱ ባህሪ ብዙ ጊዜ ጸጸትንና ቁጭትን ብቻ ነው የሚፈጥረው፡፡
በዘፍጥረት 47 ላይ ፈረኦን የያዕቆብን ዕድሜ ጠይቆት ነበረ፡፡ ‹‹..የእድሜህ ዘመን ስንት ነው? ለሚለው ጥያቄው የመለሰው ከቁጥር ጋር ክፉም ጥቂትም የሚሉ ቃላቶች ነበሩ፡፡እነዚህ ቃላት የሚያሳዩት በተለያየ ሁኔታ ስለ ተቃጠሉት ጊዜዎቹ ቁጭቱን ሲገልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ሁለት ሰባት ዓመታቶች ሚስትን ለማግባት የተፈጁ እና ንጹህ ስድስት ዓመታት ደግሞ የግልን ንብረት ለማከማቸት ያለፈ ጊዜ ነው፡፡ በርከት ያሉ የመከራ ዓመታትንም ከስደት ጋር አሳልፉአል፡፡
እድሜህ ስንት ነው ?
'' የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፡፡ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና ፡እኛም እንገሰጻለንና ፡፡''መዝ.90፤10
በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በርካታ ክፍሎች ላይ ስለ እድሜያችን የተጠቀሱት ጥቅሶች የሚያስገነዝቡን ዕድሜያችን እምብዛም የሚያደላድል ና የሚያስፋፋ ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡ በጣም ብዙ ዘመን እንደቀረው ሰው እንዳንኖር ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን የሆነ ዓላማ ግን ፈጽመን ልናልፍበት እንችላለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ዕድሜያችን ምን እንደተባለ ቀጥለን ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
-
ዘመኖቻችን እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ፡፡ መዝ.90፤9
-
በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፡፡ መዝ.39፤6
-
ህይወታችሁ ምንድን ነው ? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ሁዋላ እንደሚጠፋ እንፉዋሎት ናችሁና፡፡ ያዕ.4፤1
-
.....እንደ ተን.....መዝ.38....
-
እንደ ሸማኔ መጠቅለያ፡፡ ኢሳ.38፡12
ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረዱን ዘመኖቻችንን /'ዕድሜዎቻችንን'/ በቁም ነገር ላይ ካላዋልነው ና ለአንድ ለታለመ ዓላማ ካልተጠቀምንበት ዝም ብሎ ሊያልፍ የሚችልም ነገር እንደሆነ ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር እድሜን የሰጠን በአቅማችን ሰርተን ማለፍ ካለብን ዓላማ ጋር ነው፡፡ በተለይ ሰዎችን ከዘላለም ሞት ከማዳን ዓላማ ጋር የተያያዘው ደግሞ የላቀው ነው፡፡አለዚያ ዘመናችን ውስን በሆኑና እዚህ ግቡ በማይባሉ አልባሌ ነገሮች ሊያልቁ ይችላሉ፡፡ ስንት ነገር መስራት የሚችል አዕምሮ በዋል ፈሰስ የቀረበት፣ የተፈጠሩበትን ዓላማ ሳያሳኩ ጊዜ ያለፈባቸው፣ ኸረ እንደውም የቀበርናቸው ስንት ናቸው፡፡ ከሚያሳሳው ጉልበታቸው ጋር፣ ችሎታና ብቃታቸው ጋር ያለፉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን አሁንም ያልረፈደብን በርካቶች አለን፡፡ ቃሉ እንደሚል '' ደስ አያሰኙም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፡ ብርሐን ወደ ጨለማ ሳይቀየር...ስጋም ወደ አፈሩ ሳይመለስ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ፡፡'' መክ. 12፤1-8፡፡
ሰዎችን ከማዳን ጎን ለጎን ግን ህጻናትን የማሳደግ፣ ድሆችን የመመገብ፣ አረጋውያንን የመንከባከብ፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ጥበቃን የመሰለ፣ ሌላም ሌላም ህብረተሰብን የሚጠቅም በጎ ራዕይ ሰርቶ ማለፍ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በርካቶች ይህንን አድርገዋል፤ እያደረጉም ያሉ አሉ፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የሰዎች ዕድሜ ላይ የሚያጠና አንድ ምሁር ሰዎች የምድር ዘመን ቆይታቸው ሰባ ዓመት ቢሆን በዋናነት ዕድሜያቸውን በምን ጉዳይ ፈጅተውት እንደሚያልፉ በጥናት ካሰፈረው ነገር ቀጥለን እናያለን፡-
-
ለእንቅልፍ 23 ዓመት / 32% /
-
ለስራ 16 ዓመት / 22% /
-
የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመከታተል 8 ዓመት / 11% /
-
በመመገብ 6 ዓመት / 8.6% /
-
በመጉዋጉዋዝ 6 ዓመት / 8.6% /
-
በመዝናናት 4.5 ዓመት / 6.5% /
-
በተለያየ ህመም 4 ዓመት / 5.7% /
-
በመልበስ 2 ዓመት / 2.8% /
-
እንደ ጸሎት ያሉ የዓምልኮ ስርዐትን በመፈጸም 0.5 ዓመት / 0.9% /
በእርግጥ አንዳንዶቹ እንደየ አካባቢው ሁኔታና እንደየ ህብረተሰቡ ዓይነት ሊለያዩ የሚችሉ ነገሮች ቢሆኑም፤አብዛኞቹ ግን በብዙዎቻችን ህይወት ያጋጠሙና እያጋጠሙ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህም ውጪ ጊዜዎቻችንን በደንብ አድርገው እየጎመዱ ያሉ ነገሮች አይጠቀሱ እንጂ እንዳሉ እሙን ነው፡፡ እስኪ ጥቂት ጊዜ ወስደው የእርሶን ጊዜ በአብዛኛው እየፈጀ ያለ ጉዳይ ምን እንደሆነ ያስቡና ፡ በዓመት ያስሉት ፤ ከዚያ ወደ ሰባ ዓመት ይቀይሩት፡፡ በእርግጠኝነት አንድ ነገር ይማሩበታል፡፡ በቀን የሚጸልዩትን ሰዐት ወደ ወር ፣ ደግሞ ወደ ዓመት ቢቀይሩም በጌታ ፊት ምን ያህል ጊዜ በዘመንዎ እንዳጠፉ ማወቅ አይቸግርዎትም፡፡ የተፈጠርንበትን ዓላማ በተሰጠን ዕድሜ በትክክል ፈጽመን እንድናልፍ እግዚአብሔር ይርዳን ! ጊዜያችን በከንቱ ያለቀብንና ዕድሜያችን የገፋም ካለን ፡ ምንም የማየይሳነው ጌታ ተምችና ኩብኩባ የበላብንን ዓመት እንዲ መልስልን ብንማጸነው ፣ ወይም እንደሶምሶን አንድጊዜ እንዲያስበንና የመጨረሻ ስራ ሰርተን እንድናልፍ ብንጠይቀው መልካም ነው፡፡ በእግር ኩዋስ ዓለም ያለ ምንም ግብ 90 ውን ደቂቃ ከጨረሱ በሁዋላ፡ በባከነ ሰዐት ግብ አስቆጥረው ፣ ድል አድርገው እንደሚወጡት ቡድኖች ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነገር ሁሉ ያግዘን ፡፡ አሜን፡፡
ማስታወሻ፡- ውድ ጊዜያቸውን ለከበረ ዓላማ እንዲያውሉት ለሚሳሱላቸው ሰዎች ይህንን መልዕክት ያጋሩአቸው፡፡
አገልጋይና አገልግሎቱ
የዛሬው ፅሑፍ እ.ኤ.አ. February, 2012 በአንድ አካባቢ ለተገኙ የአብያተ- ቤተክርስቲያናት መሪዎችና አገልጋዮች ጉባኤ ላይ፡ ስለ አገልጋይና አገልግሎቱ ለሚያነሱት ሰፊ ውይይት ለመነሻነት ባቀረብኩት ጽሁፍ ላይ መጠነኛ ነገር ተጨምሮበት የቀረበ ነው፡፡
የንባብ ክፍል ገላቲያ 2፤1-10
'' ከዚያ ወዲያ ከአስራ አራት ዓመት በሁዋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአህዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኩዋቸው፤ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኩዋቸው፡፡ ''
በክፍሉ ላይ እንደ ተመለከተው ሐዋርያው ጳውሎስ እራሱንና አገልግሎቱን ያስፈተሸበት ታሪክ ነው፡፡ ከዳነ ከ14 ዓመታት በሁዋላ ወሳኝ የሚባሉ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ጠይቁዋል፡፡
1ኛ-በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን ? የሚልና
2ኛ-ደግሞ ምናልባት በከንቱ እንዳልሮጥ
የመጀመሪያው አሳብ ለዓመታት የሄደበትን፣ የደከመበትን ሩጫና አገልግሎት ማስገምገሙ ሲሆን ፣ሁለተኛው ግን ያለፉት የአገልግሎት ሩጫዎች በከንቱ የነበሩ እንኩዋ ከሆነ ፤ቀጣዩ ግን ትክክለኛና የሰመረ እንዲሆን ፣ እግዚአብሔርም የሚከብርበት እንዲሆን የታሰበ ነው፡፡ ስለዚህም እስከዛሬ ድረስ የሚሰብከውን ወንጌል ለዋነኞቹ ሐዋርያት በዝርዝር በማቅረብ ትክክል እንደሆነና እንዳልሆነ አስገምግሞአል፡፡
ለመሆኑ ሐዋርያትስ ምን አሉት? እነርሱማ ነገሩን በመንፈስ ከመዘኑት በሁዋላ በአገልግሎቱ ውስጥ የተሳሳተ ወይም ከእውነት ጋር የተቃረነ ነገር ስላላገኙበት፡ በርታ ፣ቀጥል ብለው ቀኝ እጃቸውን ሰጥተውታል፡፡በብዙ አስገራሚ መንፈሳዊ ልምምዶች ውስጥ የከረመና መለኮታዊ ሚስጥራትን በመግለጥ የሚታወቀው ፣ለበርካታ አብያተክርስቲያናት መተከል ፣መታነጽ ና ማደግ ምክንያት የሆነው፤ከዚህም ሌላ ከ13 የማያንሱ ፡ከግማሽ በላይ የአዲስ ኪዳን መጻህፍቶችን የጻፈ ሐዋርያ፣ እራሱንና አገልግሎቱን አቅርቦ ካስገመገመ፣ ቆም ብሎ ከጠየቀ? እኛማ ይልቁን እንዴት አብዝተን ማድረግ ይጠበቅብን ይሆን?
አገልግሎትን ስናስብ በ1ኛ ጢሞቲዎስ ም.3 ቁ.1 ላይ ያለው ቃል ትዝ ሊለን ይችላል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካም ስራን ይመኛል፡፡'' ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚናገሩት የዚያን ጊዜ የነበረው አገልግሎት አገልጋይነትን የሚያስመኝ ዓይነት አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለዚህም በዚያ የጠበበ በር ሾልኮ ለመግባትና እነዚያን የማይመቹ ሁኔታዎች አልፎ ለማገልገል የሚመኝ ካለ ፡መልካም እንዳደረገ ለመግለጽ ነው፡፡ ቃሉ የሚመኝ ስላለ ብቻ አገልግሎት በምኞት የምንገባበት ነው ማለት አይደለም፡፡ የተመኘም ሁሉ የሚከናወንበትም አይደለም፡፡ አገልግሎት የጥሪ ፣ የሸክም ጉዳይ ነው፡፡ የተጠሪው ብቻ ሳይሆን የጠሪውም ሙሉ ፈቃድ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
አገልጋይነት ሌሎች ለኛ እንዲኖሩ ፣ ሌሎች ለኛ እንዲሰሩ የምናዝበት ሳይሆን፤ከስሙ እንደምንረዳው ሌሎችን ማገልገል ማለት ነው፡፡ ለሌሎች መዳን ፣ጥቅምና ትርፍ መድከምን ያሳያል፡፡ ጌታችን እንደ ተናገረው '' የሰው ልጅ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡'' ብሎአል ማር.10፤45፡፡ ደግሞ በሉቃስ ወንጌል ም.22 ቁ.27 ላይ '' ..እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ ፡፡ '' ብሎ ተናግሩዋል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የአገልጋይነትን ትክክለኛ ትርጉም የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ነፍስን ቤዛ ማድረግ እንኩዋ ቢቀር ባለን ጸጋ፣ ሙያ፣ ክህሎት ሁሉ ለብዙዎች ቤዛ መሆን እና ክብርና ሙገሳን ሳይፈልጉ በሰዎች መካከል እንደ አገልጋይ መኖርን ግን ያካትታል፡፡
ከዚህ ቀጥለን አንዳንድ መንፈሳዊ ሰዎች ስለ አገልግሎት የተናገሩትን ነገር እንመለከታለን፡-
-
አንድ ምሁር ስለ አገልጋይነት የተናገረው እንዲህ ነበር '' አገልጋይ ማለት ሰዎች ሊሰሩ የማይፈልጉትን ነገር እንዲሰሩ ማድረግና ፣የሚሰሩትንም ነገር እንዲወዱት የማድረግ ችሎታ ነው '' ብሎአል፡፡
-
አንድ ሌላ ዶክተርም እውነተኛ አገልጋይ ማለት መንገዱን የሚያውቅ ፣ከመንገዱ ሳይዛነፍ ወደ ፊት የሚገሰግስ ና ከሁዋላ ያሉትንም ሰዎች ወደ ፊት የሚስብ ነው ብሎአል፡፡
-
ሞንት ጎመሪ የተባለ የጦር አዛዥ የነበረ ሰው እንደ ጻፈውም '' ሰዎችን የመማረክ ችሎታ የሚወሰነው ፡ሰውየው ባለው መልካም ባህሪያት መጠን ይሆናል፡፡ የማነቃቃት ፣የማበረታታትና ሰዎችን የመሳብ ችሎታ ካለው ሰዎችን ይማርካል'' ብሎአል፡፡ ሌሎችም በርካታዎች ስለ አገልጋይና አገልግሎት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጽፈዋል ፡ተናግረዋልም፡፡
እንዲያው ለመሆኑ አገልጋይ እና አገልግሎቱ ስንል የቱን ማለታችን ነው? የተባለ እንደሆነ፤የቃሉን ሰባኪና አስተማሪ ማለታችን ነው፤ ህዝቡን የሚመግቡ መጋቢዎችንና የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ማለታችን ነው፤ ደግሞ የጋብቻ ና የተለያዩ መንፈሳዊ ጉዳይ አማካሪዎችን ማለታችን ነው፤ የውስጥ ና የውጪ የሙሉ ጊዜ እና የትርፍ ጊዜ አገልጋዮችን ማለታችን ነው፡፡ሌሎችንም እንደ ድቁንና፣ የጸሎት፣ ዝማሬ፣ የህጻናት አገልጋዮችንና የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡
እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ስናነሳ ለዛሬ ትኩረታችን ወደ ሆነው ወደ ሌላው ተከታዩ ሐሳብ እናመራለን፡፡ብዙዎች እንደሚስማሙት አገልግሎትም ሆነ አገልጋዮች ላይ ከፊት ይልቅ ጠንከር ያለ ተግዳሮት በዝቶባቸዋል፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፣ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም አሉ፡፡ እንደውም አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደሚናገሩት ፡ አንድ የሆነ ሪቫይቫል ካልመጣ ወይም በሆነ መንገድ መለኮታዊው ጣልቃ ገብነት ካልተከሰተ በቀር፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ሊያሽቆለቁሉ ይችላሉ ብለው ይፈራሉ፡፡
መድረኮቻችን፣ የጊዜ አጠቃቀማችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውቀታችን ውስንነት፣ የንባብ ፣የጸሎት ህይወታችንና ልምምዳችን አጠቃላይ ከዕለት ዕለት እየቀነሱ እና በሌሎች ጊዜን በሚወስዱ እንደ ፌስቡክ፣ ድራማ፣ ፊልም፣ ሌሎች መዝናኛዎች እየተፈተኑ እንዳለ በርካታ ክርስቲያኖች ስለራሳቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡ የ '' መድረኮቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ '' ፀሐፊም በመጽሐፋቸው ውስጥ ሊጠቁሙን የሞከሩት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከቃሉ ውጪ የሆነ አደራረግ ና ልምምድ በዝቶአል፤ የሚያምነውም የማያምነውም አላማኝ ስለ አገልጋዮችም ሆነ ስለ አገልግሎቱም ሁኔታ አጥብቆ እየጠየቀ ነው ብለዋል፡፡ እንዲያው ባጠቃላይ የት እንደምንገኝና ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ ለመጠቆም ያህል ጥቂት ጥያቄዎችን መጠየቅ አግባብ ይሆናል፡
-
አሁን ያለው አገልጋይ ወደ ፊት ልጁ /ለልጆቹ/ እንደ እርሱ አገልጋይ እንዲሆን ይፈልጋል ወይም ይመኛልን?
-
የተሻለ የሚባልና የሚያማልል ነገር ከዓለም ቢያገኝ ጥሪዬ፣ አገልግሎቴ ይበልጥብኛል ብሎ የቀረበለትን መደለያ እምቢ ለማለት አቅም አለው ወይ?
-
ህይወት እንደገና እንዲጀምር ቢደረግ ስንት አገልጋይ መልሶ አገልጋይነትን ይመርጣል?
-
በአሁኑ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአገልጋይ ይድራሉ ወይ? በዚህስ ክብር ይሰማቸዋል ወይ?
-
የቤተ ክርስቲያን አመራርና ሽማግሌዎችን ቁጣ በመፍራት ወይም የደሞዝ መቆረጥ ስጋት ሳይሆን በጥሪና በሸክም የሚያገለግል፣ያልዳኑ ሰዎች ጉዳይ፣ደቀ መዝሙር ያልተደረጉ ምዕመናን ሰዎች ጉዳይ ፣ የተለያዩ እንቆቅልሻቸው ያልተፈታ ሰዎች ጉዳይ ዘንድሮም ከልቡ አሳስቦት የሚጸለይ እና ርምጃ የሚወስድ፣ የሚተጋ ስንት ነው?
-
ዘንድሮ በራሱ ተነሳሽነት የተሰጠውን ሀላፊነት ሁሉ በትጋት የሚወጣ ና ጌታን ሰምቶ ነገሮችን በቅን ልብ የሚያደርግ አገልጋይ ስንት ነው?
እነዚህ ነገሮች የሚመለከታቸው በትክክል ጥሪና ሸክም እንዳላቸው ተፈትሾ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ያሰማራቻቸውን ሲሆን፤ አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደሚናገሩት በትክክል ጥሪው መጥቶላቸው ሳይሆን ፡እንዲሁ ያለ እውነተኛ ሸክም ገብተው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
መቼም ለየትኛውም የሙያ ስራና አገልግሎት ለሚታጩ ሰዎች የየራሳቸው መመዘኛዎች አሉዋቸው፡፡ አንዳንድ መመዘኛዎች ወደ ሰዎቹ ወደ ራሳቸው ጥቅም የሚያደላ ሆኖ ተገኝቶአል፤ ለእግዚአብሔር ቤት በትክክል የሚያደሉና ስራው በትክክል እንዲሰራ የሚናፍቃቸው እውነተኞችም አሉ፡፡ ለሁሉም መመዘኛ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ከነገ ወቀሳ ያተርፋል፡፡ ችግሩ መመዘኛችን እውነተኛና ከጥሩ ሞቲቭ መመንጨታቸው ላይ ነው፡፡ በመቀጠል ምናልባት ይጠቅም እንደሆነ ፡አንድ ዶክተር የተማሪዎቹን ክህሎት ይመዝንበት የነበሩ ወደ ዘጠኝ ያህል ጥያቄዎች ቀርበዋል / ከአንድ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ ናቸው፡፡
-
ትናንሽ የሆኑ ነገሮችን ደህና አድርጎ ይሰራልን?
-
ቅድሚያ መስጠት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረድቶአልን?
-
የዕረፍት ጊዜውን በአገግባቡ ይጠቀምበታልን?
-
ሥራውን በንቃት መንፈስ ይሰራልን?
-
የዕድገት ዝንባሌ የሚታይባቸውን ሥራዎች መርጦ ሊጠቀምባቸው ይችላልን?
-
የማደግ ዝንባሌ ይታይበታልን?
-
ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲገጥሙት እንዴት ነው?
-
አስቸጋሪ ነገሮችን እንዴት ይፈታቸዋል?
-
ድክመቶቹን ያውቃቸዋል? ከዚያስ ምን ያደርጋል?
እኛስ እንደ አገልጋይ ለዋና ነገራችን ፣ለጥሪ ቦታ ከመስጠት አንጻር ፣ከመታዘዝ ህይወት፣ጊዜን በአግባብ ከመጠቀም አንጻር ፣ ለማደግ ከመፈለግ፣ በመከራዎችና በፈተናዎች ከመጽናት አንጻር ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በብቃት ከመወጣትና ትግሎችን በመልካም ከማሸነፍ አንጻር እንዴት ነን?
ነገሮቻችን ከላይ በተገለጸው መሰረት ነጥረው እንዳልወጡ የሚያሳብቁብን አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፡፡ ዓለም በድህረ ዘመናዊነት፣ በዘመናዊነትና በረቀቀ ዓለማዊነት በምትታመስበት ወቅት ይህም አንዳንድ ጊዜ ሾልኮ በቤተክርስቲያንም ጭምር እየታየ ባለበት ወቅት፡ የቤት ስራችንን በጊዜ ለመስራት ካልተነሳን ወደ ፊት የሚጠብቀን ተግዳሮት ቀላል አይሆንም፡፡ የእኛ ይህንን ለመመከት ዝግጅት አለማድረግ እና በነገሮች ላይ ነቅቶ ቶሎ እርምጃዎችን ያለመውሰድ፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሄዱ ያሰጋል፡፡
የምንፈራውና የምንሰጋበት ነገር እንዲብስ ያደረገው፡ በተለይ አሁን ላለው ትውልድ የቀረበለት ምርጫ በርካታ መሆኑ ሲሆን፤አብዛኞቹ ምርጫዎች እንኩዋን በህይወት ሊያኖሩት ቀርቶ፤ ተመልሶ የእውነት እና የቤተክርስቲያን ጠላት እንዲሆን ሊያደርጉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ተጠናክሮ በመጣ መንፈሳዊ መሰልና ባልሆነ ጎርፍ ትውልዱ እንዳይወሰድ ምን ማድረግ ይገባናል? ብለን ማቀድ አለብን፡፡ ቢያንስ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባል የሆነ ሁሉ በትንሹ አስርቱ ትዕዛዛትን ፣ ወንጌላትን በቅጡ እንዲያውቅ ፣ የጥምቀት ስርዐት ፣ የጌታ እራት ስርዐት ምን እንደሆነ፤ ስለ አምልኮ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ጾምና ጥሞና የምናሳውቅበት መንገድ ማመቻቸት የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡
በአሁን ሰዐት በተለይ ወጣቱ በአውሮፓ እግር ኩዋስ ተጫዋቾች ፍቅር የተያዘ ወይም በሆሊ ውድ አክተሮች ፍቅር የተነደፈ ነው፡፡ ስለ እነርሱ ማንነት ፣ሁኔታ ፣ደሞዛቸውን ፣ዝውውራቸውን እየተከታተለ ፡ ደግሞ ለሌሎች አንዳች ሳያዛንፍ እያብራራ ነው ያለው፡፡ ስለ ወንጌል እና ከላይ ስለ ጠቀስናቸው፣ ህይወቱን ስለሚጠቅሙት ጉዳይ፡ ምንም መሰረታዊ ዕውቀት አልያዘም፡፡ በእርግጥ ሁሉም የቤተክርስቲያን ችግር ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንዱ የቀረበላቸውን ማዕድ በመግፋት ነው ለዚህ የተዳረጉት፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቀረበበት መንገድም ብዙ የሚስብ ና ትውልዱን በሚማርክ መንገድ ስላልሆነ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ብቻ ለሁሉም ቢያንስ መሰረታዊውን የደህንነት ዕውቀት ፣ ጌታ ለምን እንደመጣ? ፣ለምን እንደተሰቀለ?፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሳኤው እንዳያውቅ፤ ስለ ሚከተለው እምነት ምንነት እና ምክንያት ለሌሎች የሚያስረዳበትን ዕውቀት እንዳይጨብጥ ችግር የሆነበትን ምክንያት ማወቅ አለብን፡፡ ምናልባት ቤተክርስቲያን በመጽሀፍ ቅዱስ ዕውቀት የደረጁ አስተማሪዎች የላት ይሆን? ወይስ አሁን ያሉ መሪዎች ይህ ጉዳይ ብዙም የሚያሳስባቸው ስላልሆነና በሌላ ነገር ባተሌ ሆነው ይሆን ? ወይስ ሌላ ተጠያቂ የሚሆን /ምክንያት/ ይኖር ይሆን ? እሺ ችግራችን ምንም ይሁን! ከእንግዲህ ምን እናድርግ ? ቢያንስ ጥቂት መፍትሔዎችን ቀጥሎ ፈንጠቅ ለማድረግ ተሞክሩዋል፡፡
-
አገልግሎት እየሰለቸን ሳይሆን ደስ እያለን ከሌሎች ጋር የምንሰራበትን ሁኔታዎች ቢመቻች
-
የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና የዘርፍ መሪዎች በሁሉም መንገድ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያድጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ፤ለምሳሌ በስልጠና ፣ ስነ መለኮት ትምህርት ቤት በመላክ ፣ እርስ በርስ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ፤
-
ለመሪዎችና ለአገልጋዮች ስለ አገልግሎታቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ኑሮአቸውም ማሰበ፤
-
በቤተክርስቲያን ምስባክ ላይ እየቀረቡ ያሉ መልዕክቶች ሁሉ አቀፍና የተመጣጠኑ ስለ መሆናቸው ፤ ደግሞ ጠቃሚነታቸውን በየተወሰነ ጊዜ መገምገም፤
-
የተሰማሩ ግን ጥሪና ሸክም የሌላቸውን ለይቶ ማወቅ፣ ጥሪው ያላቸውን ደግሞ ያልተሰማሩትን በተቻለ መጠን ማሰማራት የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡
-
ማስታወሻ፡- ማናቸውም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ለሆኑ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ሊልኩላቸው ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ይባርክዎ!
.የሐሳብ መበላሸት
ለሰው ልጆች ሁሉ ውድቀት ሰበብ የሆነው የህይዋን ስህተት የመጣው ሰይጣን ሐሳቡዋን አበላሽቶት ነው፡፡ 2ቆሮ.11፤3 ፡፡ ሐሳቡ የተበላሸበት ሰው ወደ ድርጊቱ ለመግባት ቀላል ይሆንለታል፤ ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የዳዊት ልጅ አቤሴሎምም ወንድሙን አምኖንን ከመግደሉ በፊት ረጅምና የቆየ የግድያ ሐሳብ አርግዞ ነበር፡፡ ጊዜውና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ደግሞ አስገደለው፡፡ 2ሳሙ.13፤2፡፡
አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሐሳብ ያድርና ድርጊቱ ሊቆይ ይችላል፤ ይህን ጊዜ መንቃት ነው፡፡ ምንም እስካላደረኩ ድረስ ንጹህ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ቀን የሚጠብቅ ክፉ ምኞት ላይ መንገስ ያስፈልጋል፡፤ እግዚአብሔር ቃኤልን ቀድሞ ያስጠነቀቀው ለዚያ ነው፡፡ ደጅህ ላይ ሐጢያት እያደባች ነው ንገስባት አለው፡፡ አለዚያ እርሱዋ ትነግስብሃለች፡፡ ያን ጊዜ ፍቃዱዋን ታደርጋለች፡፡እግዚአብሄር ወደ ቃየን መጥቶ ከነገረው ነገር የምንማረው ኀጢያት ላይ እኛ መንገስ ካልቻልን ኀጢያት በእኛ ላይ መንገስ ይጀምራል፡/ ዘፍ.4፤7/የሚለውን ነው፡፡
ያዕቆብ 1፤15 ላይ ሲናገር '' ምኞት ጸንሳ ሐጢያትን ትወልዳለች ፡ሐጢያትም ጸንሳ ሞትን ትወልዳለች፡፡ " ሞት የሚባለው /ውድቀት ሊሆን ይችላል/፤ ከመከሰቱ በፊት ውስጥን ይዞ የሚከርመው ሐሳብ /ምኞት/ ነው፡፡ ምኞት ዝም ከተባለ ቆይቶ ቆይቶ ሀጢያትን ይወልዳል፡፤ ከዚያም ወደ ሞት ያመጣል፤ ሁሉም ሂደት ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያትን፣ሞትንና ውድቀትን በህይወቱ ማየት የማይፈልግ ሰው ራሱን ማንጻት ያለበት ከውስጥ ነው፡፡ ምን አርግዣለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንዲሰጥ በቅድሚያ ሐሳብ ነው የመጣበት፡፡ '' ዲያቢሎስም ሐሳብ ካስገባ በሁአላ ''ይላል፡ ምናልባት ዲያቢሎስ ወደ አዕምሮው የላከበትን ሐሳብ መቃወም ይችል ነበር ፡፡ ምናልባትም ወደ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ሐሳብ ቀርቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም እነርሱ ተቃውመውት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ግን ሐሳቡን አስተናገደ፤ ወደ ቀጣዩ ና ከባዱ ነገርም አለፈ፡፡ ሮሜ 6፤12 ''...ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ሐጢያት አይንገስ '' ስጋችን ላይ ሐጢያት ሲነግስ እንደ ስጋ ፈቃድ ለመኖር የስጋን ነገር አዘውትረን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ /ሮሜ.8፤5/
ውስጡ የተሸነፈን ሰው ወደተገዛለት ነገር በቀላሉ መጎተት ይቻላል፡፡ ብዙ የሚያቅተው ከነገሮች ውስጥ መውጣት ሳይሆን ነገሮችን ከውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግራቸው ከግብጽ ውስጥ ወጥተው ነበር፡ ነገር ግን በቆይታ እንደታየው ግብጽ ውስጣቸው ነበረ፡፡ ስለዚህም በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ ይለናል፡፡/ሥራ.7፤39/፡፡ ከዓለም ወጥተን ግን ዓለም ውስጣችን ካለች እየዘመርን ፣ እየጸለይን ፣ ቤተክርስቲያን እየሄድን የሐጢያት ተጠቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ከሁሉ ነገር ተገልለው አንድፊቱኑ ገዳም ለገቡ መነኮሳት እንኩዋ ትልቁ ትግል የውሰጥ ነው፡፡ ከግብጽ ወጥተህ ግብጽ ግን ከልብህ ካልወጣ ችግር ነው፡፡የሎጥ ሚስት ከሶዶም በእግሩዋ ወጥታለች ነገር ግን ሶዶም ከውስጥዋ አልወጣም ነበርና እንቅፋት ሆነባት፡፡ መቀየር ፣መለወጥ ከውስጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በአዕምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ......" የሚለን፡፡ ከየ ዕለቱ ኑሮአችን እንኩዋ ብንመለከት አንድ ሰው ወተት ወይም ጎመን የሚጠላ ቢሆን፡ ከፈለገ ቦታ ቢመጣም ወይም ነጻም ቢሆን አይነካውም፡፡ ሐጢያትን ከውስጥ ስንጠላ አዩኝ አላዩኝ ከሚል መሳቀቅ እንወጣለን፡፡ በዚህም ላይ ውስጣችንን ቦርቡሮ በጊዜ ሒደት ከሚጥለን ነገር እንገላገላለን፡፡ ልክ እንደ ጎመኑ ና ወተቱ የትም ብንሆን ፣መቼም ቢሆን አንነካውም፡፡
አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ውስጡ ችግር ያለበት ሰው ያማረ ህንጻ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ቢገባ ችግሩ አያቆምም ብሎአል፡፡ የገባበት ቦታ ነገሩን ሊለውጥ ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ በጣም ወፍራምና ዕድሜ ጠገብ ዋርካ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን በሆነ ወቅት እምብዛም ነፋስ ባልነበረበት ጊዜ ነው ሌሊት ላይ ወድቆ የተገኘው ፤በጊዜው ሁኔታው ሲጠና ዛፉ በከፍተኛ ሁኔታ ውስጡ በብል ተቦርቡሮ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቅርፊት ተሸፍኖ ያለ እየመሰለ ኖረ፤ነገር ግን ባልታሰበ ቀን ወድቆ ተገኘ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደዚያ ይመስሉኛል ተሸፍነን ጠንካራ ሰዎች እንመስላለን፣ አስተማማኝ እና የመላዕክት ህይወት ያላቸው እንመስላለን፤ ምናልባት ውስጣችን ግን በብዙ እየተገዘገዘ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በየ አደባባዩ ላይ የሚሰሙት ውድቀቶቻችንም የዚህ ውጤት ይሆናል፡፡እስቲ ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ ና ነጻ እንውጣ ፡፡ ውድቀትን ብዙ ሰው ሊያየው ፣ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ያለን የውስጥ መቦርቦርና ትናንሽ ልምምዶች ግን እምብዛም አይታይም፡፡እኛው ከጌታ ጋር እንፍታው፡፡ልምምዱ ከፍ ያለ ደረጃ እንኩዋ የደረሰ ቢሆን በጾም ጸሎት በፊቱ ብንሆን የማይለወጥ ነገር ምንም የለም፡፡ ጌታ ሁሉን ይችላልና፡፡
.ራዕይ እንዴት ይጀመራል?
" ኢየሱስም ዓይኖቹን አንስቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊሊጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? አለው፡፡ ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ፡ ሊፈትነው ይህንን ተናገረ፡፡ '' ዮሐ.6፤5ና 6፡፡
በዚህ ትምህርት ብዙዎቻችሁ የተቀበላችሁትን ራዕይ ከየት እና እንዴት እንደምትጀምሩ መርህን የምትማሩበት ፡፡ ወይም ደግሞ በህይወቴ አንድ ነገር ሰርቼ ማለፍ እፈልጋለሁ ፤ግን ከየት እና ከምን እንደምጀምር አላውቅም ለምትሉ መንገድ መንገዱን ጠቁዋሚ ትምህርት ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጥያቄ ሲጠይቃቸው እንመለከታለን፡፡ ‹ህዝቡን ለማብላት እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?› በመሰረቱ እየመጣ የነበረው ህዝብ፡ ወንዶች ብቻ ተቆጥረው 5ሺህ ህዝብ ነበሩ፡፡ ሴቶችና ህጻናት ሲቆጠሩ 13 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገሩን እነዚህን ሁሉ የመመገብ የራዕይ ጅማሬ ብለን ልናስበው እንችላለን፡፡ ራዕዩ ሲታይ በጣም ሰፊ እና ገና በሐሳብ ደረጃ ያለ ነገር ነው፡፡እነርሱም ማሰብ ጀመሩ ፤ ከየት ነው የሚጀመረው? ሰዎች አንድን ራዕይ ለመጀመር ከሐሳብ ቀጥሎ የሚያነሱት ጥያቄ አላቸው፡፡እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሙዋሉ ድረስ ምንም ነገር መጀመር ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ የሚጠይቁዋቸው ወሳኝ የሆኑ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ፊሊጶስና እንድርያስ ጠይቀውልናል፤ ወይም በራዕይ ጅማሬ ላይ ሊነሱ የሚገባቸውን ቁልፍ ሁለት ሐሳቦችን አንስተውልናል ፡፡ ቀጥለን እንዳስሳቸዋለን፡፡
ሀ. ለራዕዩ የሚያስፈልግ ነገር ሲሙዋላ መጀመር...?
ፊሊጶስ፡- '' ፊሊጶስም እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኩዋ እንዲቀበሉ የ 200 ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት፡፡ ቁ.7፡፡ በዚያን ጊዜ ከጌታ የተሰጣቸውን አንድ ፕሮጀክት ወይም ራዕይ ለመጀመር የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል ነው አስልቶ የተናገረው፡፡ 200 ዲናር በጊዜው በጣም ብዙ ብር ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ያህል፡ ጌታ ኢየሱስን አሳልፎ ለጠላቶቹ ለመስጠት ይሁዳ ከካህናት አለቆች ጋር የተደራደረበት ብር 30 ብር ነው፡፡ በዚህ ብር በዚያን ጊዜ እንጀራ ቀርቶ መሬት እንኩዋ የሚገዛበት ብር እንደነበረ ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ጌታውን የሸጠበትን ገንዘብ በቤተ መቅደስ ሄዶ በተነ፤ ነገር ግን መሬት ገዙበት፤ ቦታውም አኬልዳማ ተባለ ፤የተባለው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ 30 ብር በጊዜው እንዲህ ትልቅ ከነበረ፡ 200 ብር ምን ያህል ይሆናል? የፊሊጶስ ሒሳብ ለሰው አዕምሮ ትክክል ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለመመገብ ይህን የሚያክል በጀት አስፈላጊ ነው ማለቱ፡፡
ለ. ራዕዩን በእጅ ላይ በተገኘው ነገር መጀመር......?
እንድርያስ፡-''..አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሳ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል፡፡ '' ቁ.9 ፡፡ ይህ ሁለተኛው የአማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ፈንድ ተፈላልጎ፡ አልያም በሆነ መንገድ ከሚገኝ ካፒታል መጀመር የማይቻል ከሆነ፡ ምናልባት እጃችን ካለው ጥቂት ነገር መጀመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም ካልሆነስ ነው ጥያቄው? ፐሮጀክቱ ያቀፈው ህዝብ በሺህ የሚቆጠር ፡ በእጃቸው ያለው መነሻ ካፒታል ደግሞ ለአንድ ለሁለት ሰው ብቻ የሚበቃ፡፡ 'ይህ ምን ይሆናል ? ' አለ እንድርያስ !
በነገራችን ላይ በርካታ ራዕዮችና ውጥኖች ሳይሰራባቸው ተቀምጠው ያሉት፡ በነዚሁ ሁለት ግዙፍ ጥያቄዎች ውስጥ ወድቀው ነው፡፡ መነሻ ካፒታል ሲታሰብ ፣ ለመነሻ የሚሆን ብር ሲጠበቅ አይሞላም፡፡ ስለዚህም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡ ቤሳ ቤስቲ የሌላቸው ሰዎች ከመሬት ተነስቶ 200 ዲናር ከየት ያመጣሉ? ሌላው ደግሞ እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም የማይበቃ መሆኑ ነው ፡፡ በተለይም ከታሰበው ራዕይ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነው፡፡ ጀምሩት ቢባል እየቆረሱ ድንገት ቢያልቅስ ? ፣ ጀምሮ መዋረድ አይሆንም ? አዕምሮ ያለው ሰው ይህንን ሊያደርግ ይችላልን ? ስለዚህም ነው በሁለቱም ጎራ የተነሱት ሐሳቦች ብዙዎቻችንን ይወክላሉ ብዬ የማምነው፡፡ ሁለቱም ነገሮች ከባባዶች ናቸው፡፡ ሙሉ የፐሮጀክቱን መነሻ ካፒታል ማግኘትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ካላችሁ ነገር ጀምሩ ማለትም በሁዋላ ላይ የሚመጣውን መዘዝ በማሰብ የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ የጌታ ሐሳብ ለመሆኑ ምንድን ነው?
ከየትን እንጂ በምንን አታስብ !
ታስታውሱ እንደሆነ ሲጀመርም የጌታ ጥያቄ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? ነው እንጂ በምን እንገዛለን? የሚል አልነበረም፡፡ ለጌታ በምን? የሚለው አያስጨንቀውም፡፡ ስለዚህም ነው በምን? ን ትቶ ከየት? የሚለውን የጠየቀው፡፡ ሰው ደግሞ በምን? የሚለው ሳይመለስለት ከየት? ወደሚለው ቀጣይ ነገር ውስጥ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለ ዚህም ነው ሳይጠየቁ ሒሳብ መስራት የጀመሩት ፡፡ ለተሰጠ ራዕይ ሁሉ የሰው አስተሳሰብ ይኸው ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲመለስለት የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ካልተመለሰለት በቀር መጀመር ይፈራል፡፡ ጌታ ደግሞ እርሱን ለእኔ ተወውና ከየት እንደሚገዛ ንገረኝ ይላል፡፡ በተለይ '' እራሱ ሊያደርገው ያለውን ነገር አውቆ ይህን አለ፡፡'' የሚለው ቃል አስደናቂ ነው፡፡ ምንም ወደ ሌላቸው ሰዎች ትልልቅ ራዕይ ሲያመጣ እርሱ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ ሊያደርግ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ ነው ፡፡ በቅድሚያ በጀቱን ሰጥቶ ሂዱና ህዝቡን አብሉ!፤ ይህንና ይህን ስሩ! ቢለን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደዚያ አይሆንም፡፡
ለመሆኑ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገሮች ፡ማለትም ፊሊጶስ ካቀረበውና፡ እንድርያስ ካቀረበው ሐሳብ፡ ጌታ የትኛውን መረጠ ? ወይም ምን አደረገ ? የሚለውን ነገር ከቃሉ ላይ አብረን እንመልከት፡፡ '' ኢየሱስም ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ አለ፤በዚያም ስፍራ ብዙ ሳር ነበረበት፡፡ወንዶችም ተቀመጡ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር፡፡ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፡አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፤ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡዋቸው፡፡ ''ቁ.11-12
እንዳነበብነው እጃቸው ላይ ያለውን ያውም የራሳቸው ያልሆነ ግን በመካከላቸው የተገኘ የአንድ ብላቴና እራትን ተጠቀመበት፡፡ አመስግኖ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፡፡ በአዕምሮአችን ውስጥ መሀል ላይ ቢያልቅስ? ፣ ባይዳረስስ? ....ወዘተ የሚሉ አሳቦች ይኖራሉ ፡፡ ነገር ግን እነርሱን እንተዋቸው፡፡ ዝም ብለን ባለን ነገር እንጀምር፡፡ አርሱ አያሳፍረንም፡፡ በጣም መጠንቀቅ ያለብን ፡ መነሻ ላይ ማነው የተናገረኝ? የሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡ራዕዩ የትኛውንም ያህል ትልቅ ይሁን እግዚአብሔር ተናግሮን ከሆነ መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለህዝቡ ቆርሰው ማደል ጀመሩ ፤ አይናቸው እያየ ሁሉ እንደሚፈልገው መጠን ወስዶ ፣ጠግቦ ፣ የተረፈውን ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞሉ፡፡ የኛ ጌታ እንደዚህ ነው ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት ከመነሻህ ጋር ማመሳከር እስኪያዳግት ድረስ የሚባርክ አምላክ ነው፡፡
በጣም ትልልቅ ነገር የሰራባቸውን ሰዎች ምስክርነት መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ዎርልድ ቪዥን ዛሬ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ከመድረሱ በፊት፡ መነሻ ካፒታሉ ቦብ ፒየርስ የሚባል የድርጅቱ መስራች በወንጌል ምክንያት የተሰደደችን አንዲት ብላቴና በጊዜው ከረዳበት አምስት /5/ የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ ጋሽ በቀለ ስለ ዎርልድ ቪዥን በጻፈው መጽሐፉ ላይ ታሪኩን አስፍሩዋል፡፡
ከብዙዎች ንግግር እንደተረዳሁት ሁሉም ክርስቲያኖች ማለት ይቻላል፡ በተለይ ከሆነ ጊዜ በሁዋላ በህይወታቸው አንዳች ነገር ሰርቶ የማለፍ ጥማት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ግን ከየት? እና እንዴት? እንደሚጀምሩት አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ብዙ ህጻናትን የማሳደግ እና አዛውንቶችን የመንከባከብ አልያም ሌሎች በጎ የልማት ስራዎችን ስለ መስራት አስበው ከሆነ ፡ ቢያንስ ከአንድ ህጻን ወይም አንድ አዛውንትን ከመርዳት መጀመር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ከቆይታ በሁዋላ ስራው /ራዕዩ/ እየሰፋ ይሄድና ለብዙዎች ጥላ ለመሆን ይበቃል፡፡ ራዕዩ ከጌታ ይሰጠን እንጂ፡ ያለንን ጥቂት ነገር ባርኮ መጀመር ብቻ ነው ፡፡
ጥርት ያለ ራዕይ ተቀብለው : ለመጀመር ሚሊዮን ብሮችን ሲጠብቁ ሲጠብቁ ፡ ራዕያቸው አጀንዳቸው ላይ ብቻ የቀረባቸው አያሌዎች ናቸው፡፡የምንፈልጋቸው ውጤቶች ስንጠብቃቸው ሳይሆን እየሰራን እያለ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ከመጠበቅ መንፈስ ወጥተን ፡ባለን ነገር እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ፡፡ ነገሮች እንደ መብረቅ ድንገት ላይከሰቱ ይችላሉ፡፡ ትልልቅ ነገሮችን እጃችን ባለው ትንሽ ነገር እንጀምራቸው ፡፡ ነገ ትልቅ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ አንዳንዶቻችን ይህ እውቀት ጎድሎን ነው ነገራችንን ያዘገየነው፤ አንዳንዴም ያበላሸነው፡፡ እስኪ ዛሬ እንደገና ለመነሳት እንሞክር ፤ ዓላማችንን አንስተን በእምነት እንጀምር፡ መክሊታችንን ሳንነግድበት ጌታ ድንገት እንዳይመጣብን እፈራለሁ፡፡ ነገ ዛሬ ሳንል ስንፍና መጥቶ እንደ ወንበዴ ሳይከበን፣ ምክንያቶቻችንን ሁሉ ጥለን፡ ራዕያችንን ለመፈጸም እንነሳ፡፡ ቢያንስ እኮ አንድ ለወንጌል ልቡ የሚቃጠልበትን የገጠር ወንጌላዊ መርዳት፣ አንድ ወይም ሁለት ልጆችን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት መነሳት፣ ወይም በተለያየ ጊዜ ከቡና ቤት በወንጌል አምነው የወጡትን ሌላ ስራ እስኪይዙ ድረስ ኑሮአቸውን ማገዝ፣ ወይም አንድን ድሀ ቤተሰብ ፈልጎ መርዳት፣ ወይም ትራክቶችን ማሳተም....ወዘተ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ በጣም ብዙ ብዙ በጎ ራዕዮች አሉ፡፡ እባካችሁ እንፍጠን!!!
ማስታወሻ፡- አስተያየት ካላችሁ በአድራሻው /ከታች ባለው ኢሜይል/ ሐሳባችሁን መጻፍ ትችላላችሁ፡፡ ሳንሰበሰብ በፊት ራዕያችንን እንድንፈጽመው ጌታ በቀሪ ዘመናችን በነገር ሁሉ ይርዳን፡፡ አሜን!