top of page

የጦር አዛዡን ስለ ታደገች ብላቴና !

 

ታ ሪኩ እውነተኛ እና ታላቁ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው፡፡ ከስንት ጊዜ በፊት ሶርያውያን ከእስራኤል ጋር ባደረጉት ጦርነት ወቅት ሶርያውያን አንድ ብላቴና ማርከው ወደ አገራቸው ወሰዱ፤ ንዕማን በተባለ የአገሩ የጦር አዛዥ ቤት እንድትሔድና ሚስቱን እንድታገለግል ትደረጋለች፡፡ በዚያም ሳለች ንዕማን ምንም የተከበረ፣ ጀግናና ጽኑ ሰው ቢሆንም ነገር ግን ለምጻም ስለነበር በጣም ታዝንለታለች ፡፡ ለእመቤትዋም '' ጌታዬ በሰማርያ ካለው  ከነብዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት፡፡'' 2ነገስት 5፡3

 

እመቤትዋም ይህንን መልካም ወሬ እንደሰማች ለባለቤትዋ ለንዕማን ትገግረዋለች ፡፡ ቀን ተቀጥሮ ና ተዘጋጅቶም ወደዚያው ያቀናል፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ለምጹ ተፈውሶ ፣ ከእግዚአብሔር ውጪም ከእንግዲህ ሌሎች አማልከቶችን ላለመከተል ቃል በመግባት ወደ አገሩ በሰላም ይመለሳል፡፡ የዘመናት ችግሩና ጥያቄውም በዚያው ቀን ተመለሰላት፡፡

     ከዚህች ትንሽ ብላቴና ምን እንማራለን?

  • የምታውቀውን ፈዋሽ ነብይ አስተዋወቀች፤

  • ያለችበት ሁኔታ: ምርኮኛ መሆን፣ ብላቴና መሆን፣ ሰው ቤት መሆን...ወዘተ ያላገዳት ሴት ነች፡፡

  •  እኛስ እንዴት ነን? ለሰው ልጆች ሁሉ መድኀኒት ስለ ሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ላለመናገር ሰበብና ምክንያት ይኖረን ይሆን?                                                                           

 

      ከጦር አዛዡስ ሕይወት ምን እንማራለን?

  • በቅድሚያ የዚህ ችገር /ለምጽ/ ተጠቂ ነኝ ብሎ ማመኑ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ዛሬ በርካታ ሰዎች የብዙ ሱስና ሐጢያት ተጠቂ ሆነው ግን ምክንያት ና ሰበብ ያበጁለታል እንጂ ይህ ችግር አለብኝ ብለው በግልጽ አያምኑም፡፡ ስለዚህም ፈውሳቸው ይዘገያል፡

  •  ሌላው ደግሞ ምንም ትልቅ ባለስልጣን ቢሆንም ከትንሽ ልጅ ለመስማት መዘጋጀቱ እና የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሰሙት እውነት ቶሎ ምላሽ የሚሰጡ ነዎት?

  •  ያደረገለትን እግዚአብሔርን አመሰስገግናኗለል፤ ከእስራኤል አምላክ ውጪም ሌላ አማልክቶችን ላለመከተል ቃል ገብቶአል፡፡ሌሎች እንዳዳኑት አስመስሎ በግብዝነትም አልቀረበም፡፡

 

ልብ ይበሉ፡ ዛሬም በፍጹም ልባችን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ብንቀርብ በስጋችን ካለ ከየትኛውም ዓይነት  ችግር እና በነፍሳችን ደግሞ ከዘላለም ሞት ይታደገናል ፡፡

                ኢየሱስ ክርስቶስ የስጋም የነፍስም ፈውስ ነው!!!

 

ለቪዛ ፈላጊዎች

 

  የተለያዩ ሰዎች ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ለማሸነፍ  በርካታ መንገዶችን ተጠቅመው ከአገር ይወጣሉ፡፡ አንዳንዱ ህጋዊነትን ተከትሎ የሚፈጸም ሲሆን፡ በተቃራኒው ህጋዊነትን ባልተከተለ መንገድ ለብዙ እንግልትና ስቃይ እየተዳረጉ አገር የሚቀይሩም ዜጎች አሉ፡፡ ይህም በዋነኝነት ሁሉም ሰው የሚፈልገውን  የቪዛ ጥያቄ እንደሚፈልገው ስለ ማይፈቀድለት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቪዛ  የሚፈቀድበት የራሱ መስፈርትና አሰራር አለው፡፡

 

   ይህ ሲባል ግን ትክክለኛ ቪዛ ያገኙ ሰዎች የሚሄዱበት ምድር ችግር አይገጥማቸውም ማለት አይደለም፡፡ እዚሁ ዓለም እስከሆነ ድረስ የትም አገር ቢሆን የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ አንደየ ቦታው ሁኔታ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡

በእርግጠኝነት ቪዛ ሊያገኙበት የሚችሉበት፣ በሚሄዱበት አገርም ምንም አይነት ችግር የማይገጥሞዎት አንድ አገር ብቻ ነው፡፡ይህን ዕድል ለመጠቀም ከፈለጉ በጥንቃቄ ቀጣዩን መስፈርቶች ይከታተሉ፡፡

 

መጽሐፍ ሲናገር  ''...ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤....ሞት ከእንግዲህ አይሆንም ፡ኀዘንም ወይም ጩኸት ወይም ስቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፡፡'' ራዕይ 21፡1-4፡፡ በዚህ አዲስ አገር ውስጥ ምንም ችግርና ሰቆቃ የሌለ ሲሆን ደስ በሚል ብርሐን ውስጥ ሰላምና ዕረፍት አግኝቶ ከዘላለም እሰከ ዘላለም ድረስ መኖር ያስችላል፡፡

 

    ቪዛውን ታዲያ እንዴት ማግኘት ይቻላል?

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁ.16-21 ያንብቡ፡፡ በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ይመኑ! እርሱም ስለ እኛ ሐጢያት የተሰቀለ፣ የሞተ፣ በሶስተኛውም ቀን የተነሳ ነው፡፡ ልክ  ስለ  እርሶ የሞተውንና  የተነሳውን  ክርስቶስን  አምነው  ንስሐ  ሲገቡ ፡ ስምዎ  በህይወት  መጽሐፍ  ላይ ይጻፋል፤  የመንግሰተ  ሰማይ  መግቢያ  ቪዛውን ም ይቀበላሉ፡፡

 

       ለጥንቃቄ

  • ይጠንቀቁ! ቪዛውን እኛ እንሰጣለን የሚሉ ክርስቶስ የማያውቃቸው ና ህጋዊውን መንገድ የማይከተሉ በርካታ ሐይማኖታዊ ድርጅቶችና አገልጋዮች አሉ፡፡ መንገዱ አንድ ብቻ ነው እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐ 14 ቁ.6፡

  •  ንስሐ ገብተውና ተዘጋጅተው ፣ በማመን ያገኙትን የመዳን ቪዛ ይዘው ጌታ እስኪገለጥ ድረስ በእምነት ጸንተው ይጠብቁ!

 ቃሉን /መጽሐፍ ቅዱስን/ ያንብቡ ፣ በየዕለቱም ይጸልዩ!

 የሠርግ ጥሪ

  የማክበር ሰላምታችንን እያቀረብን ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር በፊታችን ባለው አንድ ቀን ሙሽራው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽሪትን /ቤተክርስቲያንን/ ከምድር ሊወስዳት ይመጣል፡፡ ልብ ይበሉ የሚመጣበት ሰዐትና ቀን  ባለመገለጹ / ማቴ.24፡36/ ከዛሬዋ ቀን ጀምረው በእውነተኛ ንስሐ ተዘጋጅተው ሙሽራውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ሙሽራው በሚመጣበት  ያን ጊዜ የዓለም መጨረሻው ይሆናል፡፡ 

 

       በዚህ ሰርግ ላይ ለመታደም የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፡-

 

1- ነጭ ልብስ መልበስ አለብዎት፡፡ ማቴ 22 ቁ. 11-14 ይህም ንስሐ ገብተው በክርስቶስ ማመንዎትን የሚገልጥ ነው፡፡

 

2- መብራትና በቂ የሆነ ዘይት መያዝዎትን አይዘንጉ፡፡ ማቴ.25፡1-13

 

3- ታማኝነትና ልባምነት፡፡ ማቴ.24፡45-51፡፡ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

 

ታዲያ እርሶ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ አምነዋልን? እውነተኛስ ንስሐ ገብተዋልን ? ዛሬውኑ ይወስኑ!!!

                                           Maranatha!

 የመኖሪያ ቤት ምዝገባ

 

‹‹ ልባችሁ አይታወክ ፤በእግዚአብሔር እመኑ፡ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፡፡ እንዲህስ ባይሆን ባልኩዋችሁ ነበር ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፡፡ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፡ ወደ እኔም እወስዳችሁዋለሁ፡፡›› ዮሐ.14፡1-3

 

  በስማችን የተመዘገበ የምድራዊ መኖሪያ ቤት ሊኖረንም ላይኖረንም ይችላል፡፡ ቢኖረንም በጣም ጥቂት ጊዜ የምንኖርበት ነው፡፡ እኛም ቢሆን ቤቱ ያልፋሉና፡፡ ትልቁ ጉዳይ በዘላለም ቤት በመንግስተ ሰማይ ቤት የሌለን እንደሆነ ነው፡፡

 

       ለዘላለም  ቤት  እንዲኖርዎ  ምን  ማድረግ  አለብዎ?

1. የዘላለም መንገድ ፣እውነት እና ህይወት በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን!

   ቃሉ እርሱን ክርስቶስን ብንክደው እርሱም ይክደናል ይላል፡፡ 2 ጢሞ.2፡12

 

2. ከሐጢያትዎ ሁሉ በንስሐ ተመልሰው ፡ መልካም ፍሬን ማፍራት፡፡

 

3. በቀሪ ዘመንዎ በፍጹም ልብ ክርስቶስን ለመከተል መወሰን፡፡ ይህን ሲያደርጉ ህይወትዎ ይለወጣል፤ የዘላለም ቤትም በሰማይ ይዘጋጅልዎታል፡፡

 

ማስታወሻ፡-ይህንን መልዕክት ለሌሎች ሼር ያድርጉ! 

 አፋልጉኝ

 

  ልብ ብለው ያንብቡ፡፡ ምንም እንኳ ክርስቶስ  የዓለም መድኀኒት ሆኖ የጠፉትን በጎች ፍለጋ  ቢመጣም እሺ ብለው የታዘዙትና ያመኑተት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ከመንግስቱ እርቀው ነው ያሉት፡፡ ስለሆነም ዋጋ የከፈለላቸውን እነዚህን  ተቅበዝባዥ ህዝብ ካሉበት ቦታ እየፈለጉ በወንጌል መልዕክት ወደ መንግስቱ ለሚያመጡ እውነት እላችሁዋለሁ ዋጋቸው አይጠፋም፡፡

 

                     የጠፉ ሰዎች ልዩ ምልክታቸው

 

·        1-   ሰላም የላቸውም ፣ ትርጉም ሌለው ኑሮ እየኖሩ እንደለ ያውቃሉ፣ በብዙ ጉዳይ ደስታ ከህይወታቸው ስለጠፋ ዘውትር ይጨነቃሉ አንዳንዶቹ እንደውም የክርስቶስን ወንጌል በግልጽ ይቃወማሉ፡፡

      '' መዳን በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ ከሰማይ የተሰጠ ስም ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ማንም የለም፡፡'' ሐዋ.4፡12 :: የሚለውን  ያልተረዱ ናቸው፡፡

 

 2-    ከሐጢያታቸው በንስሐ ከመመለስ ይልቅ ምኞታቸውን ለመፈጸም ሰበብ ያበዛሉ፡፡

 

 3-   ዓለምንና በዓለም ያለውን ነገር በመውደድ የተጠመዱ ናቸው፡፡

 

  ሰዎችን በፍቅር ቀርበን ወንጌልን በመስበክ ከሐጢያት መንገድ እንመልሰቸው!

 

''  ወቀረበ ኢየሱስ ወተናገርሙ እንዘ ይብል ተውህበ ሊተ ኩሉ ኩነኔ ሰማይ ወምድር ሑሩ መህሩ ኩሉ አህዛብ እንዘ ታጠምቅዎሙ በስመ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ ቅዱስ ወመህርወሙ ኩሉ ያዕቅቡ ዘአዘዝኩክሙ፡ ወናሁ አነ ምስሌክሙ በኩሉ መዋዕል እስከ ኅልቀተ ዓለም፡፡''  ወንጌል ዘ ማቴዎስ 28፡18-20

  ነጻ የትምህርት ዕድል  

 

  በህይወትዎ በአጭር ጊዜ ለውጥን የሚያመጣ ትምህርት የቱ ነው ?ከትምህርቱ በሁዋላ ከእርስዎ የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው ?'' እነዚህን አስተምርና ምከር ፡፡ ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን በትዕቢት ተነፍቶአል፡ አንዳችም አያውቅም፡፡ ''1ጢሞ. 6፡3ከላይ እንደተጠቀሰው ፡-

 

1. መማር ያለብዎት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ጤናማ ቃል ሲሆን፡ ይህም ጌታችን በአካል ሲያስተምር የነበሩ ሐዋርያት ተከታትለው የዘገቡት ወንጌላትና ፡ መልዕክታትን ማንበብ ይጠበቃል፡፡ የእግዚአብሔር ሐሳብ የሰፈረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡

 

2. ትምህርቱን ከተረዱ በሁዋላ ማድረግ የሚጠበቅብዎት ነገር፡ እግዚአብሔርን ለመምሰል መለማመድ ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔርን መሆን ማለት ሳይሆን እርሱ እንደሚፈልገው እንደ ቃሉ ሆኖ መገኘት ነው፡፡

 

መማር የሌለብን ትምህርት ምንድን ነው?

 

ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የተጻፉ ብዙ የሰው ድርሰቶችና ገድላቶች ስላሉ፡ አራስዎን ከዚያ መጠበቅ አለብዎ፡፡ሲጀመር እግዚአብሔርን ለመምሰልና ለዘላለም ህይወት ሊጠቅሙን ቀርቶ ፡ጭራሹን የሚያጎድሉንና ከእውነት የሚያስቱ ናቸው፡፡ ሲቀጥል እውነተኝነታቸው በታሪክ ያልተረጋገጠላቸው እና ለምድራዊ ህይወታችን እንኩዋ የማይበጁን ናቸው፡፡

ሐዋርያቱ ከሰበኩልን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆነው ወንጌል የሚለይ ወንጌል የሚሰብክ ፡ የሰማይ መልዐክ እንኩዋ ቢሆን የተረገመ ይሁን፡፡ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን፡ ተብሎአል፡፡ ገላ.1፡8-9 እውነተኛ ንስሐ ይግቡ ! መጽሐፍ ቅዱስዎን ያንብቡ!

 

ማሳሰቢያ፡- ተጨማሪ ማብራረያና ትምህርት ከፈለጉ በሚከተሉት አድራሻዎች መጠቀም ይችላሉ፡፡ Info.lemekeru@gmail.com ወይም benjabef@gmail.com ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማግኘት http://tehadesothought.blogspot.com

 አዲሱ መድሐኒት

 በዓለም ላይ የተወሰኑ በሽታዎች እስካሁን በምርምር መድኃኒት ሊገኝላቸው አልቻለም ፡፡ በዚህ ምክንያት ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የዓለም ህዝቦች በስቃይና በእንግልት ላይ ይገኛሉ፡፡መድሐኒት የተገኘላቸውም በሽታዎች ቢሆኑ ከበሽታው ቶሎ አለመገኘት፣ ከመድሐኒት አወሰሳሰድ ችግር እና ጊዜያቸው ባለፈባቸው መድሐኒቶች ችግር የተፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም፡፡

 

ከበሽታዎች ሁሉ በጣም የከፋው የነፍስ ህመም ነው፡፡ ምንም እንኩዋ መድሐኒቱ ከተገኘ የቆየ ቢሆንም ብዙዎቹ ባለመውሰደቸው ምክንያት እስካሁን በነፍሳቸው እንደታመሙ ናቸው፡፡በአሁኑ ወቅት  በዓለም ላይ 3.6 ቢሊዮን የሚሆነው ህዝብ ስለዚህ መድሐኒት አልሰማም ተብሎ ይገመታል፡፡ የመድሐኒት እጥረት የለም ፤ግን መድሐኒቱን የሚሰጥ እና የሚያስተዋውቅ ባለሙያ እጥረት አለ፡፡

 

  ነፍስን እስከወዲያኛው ስለሚያሰቃየው ና መንስኤ ስለሆነው ሐጢያት ታላቁ መጽሐፍ እንደዚህ ይላል'' በበደላችሁና በኀጢያታችሁ ሙታን ነበራችሁ፡፡ ኤፌ.2፡1 ደግሞ '' ሁሉ ሐጢያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል'' ሮሜ.3፡23:: ይሁንና ለሐጢያት ደግሞ መድሐኒት ተገኝቶለታል፡፡ መድሐኒቱም ስለ እኛ የተሰቀለውና የሞተው ደግሞ የተነሳው  መድሐኒአለም ነው፡፡

 

    የመድሐኒቱ  አወሳሰድ

 

  መጀመሪያ ሐጢያትን ሁሉ መናዘዝ ነው፡፡'' ኀጢያት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም ፡፡ በኀጢያታችን ብንናዘዝ ኃጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡ '' 1ዮሐ.1፡9፡፡ ሐጢያትን ሁሉ የሚያነጻ ደም በቀራንዮ መስቀል ላይ ፈሱአል፡፡  በመቀጠልም ስለ እኛ የሞትውንና የተነሳውን መድሐኒት ክርስቶስን ማመን ነው፡፡  ይህን ሲያደርጉ ከሐጢያትዎ ሙሉ ለሙሉ ይነጻሉ፡፡

 

     ታዲያ እርሶ ንስሐ ገብተዋልን?         

       የመዳን ቀን አሁን ነው!

 ክፍት የሥራ ቦታ

 እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ የፈቀደው ስራ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

''...ይህ የእግዚአብሔር ስራ እርሱ  በላከው  እንድታምኑ ነው፡ ...፡፡ '' ዮሐ.6፡29

 

'' እርሱ ' '- የተባለው ሁሉን የፈጠረ አምላካችን እግዚአብሔር አብ ሲሆን  '' የተላከውም '' አንድያ ልጁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ነው፡፡

 

የእኛ ድርሻ፡- በአባቱ ተልኮ ወደ ምድር በመምጣት፣ በቅድስት ድንግል ማርያም ማህጸን ተወልዶ፣ ተሰቅሎ ፣ ለሐጢያታችን ስርየት እንዲሆን ክቡር ደሙን አፍስሶ፣ ሞቶ፣ በሶስተኛው ቀን ተነስቶ ደግሞ በ 40ኛው ቀን ያረገውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማመን ነው፡፡

 

 ልብ ይበሉ ለእርስዎ የተዘጋጀልዎ የእግዚአብሔር ስራ በልጁ በክርስቶስ ማመን ነው ! በእርሱም የሚያምን መጽሐፍ እንደሚል የዘላለም ህይወትን ያገኛል ዮሐ.3፡16 ፡፡ ለምድራዊ ኑሮዎ ግን ምድራዊ ስራ መስራት ሐጢያት አይደለም፡፡

 

      ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ያድናል!

© 2016 by AL Consulting LLC. Proudly created with Wix.com

  • Twitter Classic
  • c-facebook
bottom of page