top of page

 

.ሚስጥረ ቁርባን

 

''ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባርኮ ቆርሶም ሰጣቸውና እንካችሁ ይህ ስጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው ሁሉም ከእርሱ ጠጡ፡፡ እርሱም ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፡፡ '' ማርቆስ 14:22-23

  በተለያየ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች

  • ስጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት ያገኛል፡፡ ስለሚል ቁርባን ያጸድቃልን ?

  • ቅዱስ ቁርባን በቅዳሴ ጊዜ ወደ እውነተኛ የክርስቶስ ደምና ስጋነት ይቀየራልን ?

  •  ስጋውና ደሙን መውሰድ ያለበት ማን ነው? የሚሉትና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳስሳለን፡፡

   በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከተደነገጉት 7 ዓይነት ሚስጥራት መካከል አንደኛው ሚስጥረ ቁርባን በመባል ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ቁርባን  ወይም የጌታ እራት ብለን የምንጠራው ስርዓት የተደነገገው በጌታ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡበት ዕለት ጀምሮ እንዲፈጽሙት በእግዚአብሔር የታዘዙ በመሆኑ እስከዛሬ ድረስ ይጠብቁታል፡፡ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን የአዲስ ኪዳን ጥላ በመሆኑ ና ክርስቶስ የገዛ ደሙን አፍስሶ ከሐጢያታችን አጥቦ ከዓለም ስላወጣን አርነታችን እውነተኛ ፋሲካ ክርስቶስ ሆኖልናል፡፡ ስለዚህም በጌታ እራት ጊዜ በድምቀት የምናስታውሰው ትልቁ ነገር የጌታ ሞትና ትንሳኤ ነው፡፡ የፋሲካ እውነተኛ ትርጉሙም ስለ ሐጢያታችን የሞተው የእግዚአብሔር በግ ክርስቶስ ነው፡፡

  ከጊዜ ወዲህ ግን ስለ ጌታ እራት ወይም ስለ ቅዱስ ቁርባን የሚሰጡ ትርጉሞች እንደየ ቤተ እምነቱ ሁኔታ መለያየትን አምጥቶአል፡፡ ለመሆኑ የጌታን እራት በመውሰድ ይጸደቃልን ? ይህ ዋነኛ ጥያቄ በቅድሚያ መመለስ አለበት፡፡ ብዙዎች የጌታን እራት በመውሰዳቸው ምክንያት እንደሚጸድቁ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጽድቅን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን እውነት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ፅድቅ እንዴት ይገኛል? ብለን በሌላ ትምህርት ላይ አንስተን እንደነበረ ልብ በሉ ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን ጽድቅ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ነው፡፡ ዮሐ.3፤16፣ ሮሜ.6፤20፣ ሮሜ 10፤9፡፡ ታዲያ '' በስጋዎ ደሙ ይጸደቃል'' የሚለው ትምህርት ከየት የመጣ ነው ? ካልን በዮሐንስ ወንጌል 6 ላይ ከተጠቀሰው ቃል መነሻ ተደርጎ እንደመጣ የሚታመን ሲሆን ቃሉም '' ስጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው አለ፡፡'' ቁ.54 ይላል፡፡

   ክፍሉን በጥንቃቄ ብናጠና ከመጀመሪያው ጀምሮ ስለ ምን እንደሚያወራ መመልከት ይቻላል፡፡ ከቁ.1-14  ብዙ ሰዎች ፡ማለትም ሴቶችና ህጻናትን ሳይጨምር ወንዶች ብቻ 5 ሺህ  ሆነው ወደ ጌታ የመጡበት ፣ከዚያም 2 ዓሳ ና 5 የገብስ እንጀራን ባርኮ ሁሉም እንደሚፈልገው ወስዶ ጠግቦ 12 ቅርጫት ቁርስራሽ የተነሳበት ታሪክ እናነባለን፡፡ ከዚያ ቁ. 15 ላይ ህዝቡ ኢየሱስን በድንገት ነጥቀው  ለማንገስ ሐሳብ እንዳላቸው አውቆ ከእነርሱ ፈቀቅ እንዳለ ያስረዳል፡፡ ከቁ.16 እስከ 25 ድረስ ህዝቡ በተለያየ ቦታ ፈልገው ፈልገው ፡በሁዋላ ላይ ግን እንዳገኙትና አንድ ጥያቄ እንደጠየቁት ተጽፉዋል፡፡ '' መምህር ሆይ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ እውነት አውነት እላችሁዋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለበላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም፡፡ለሚጠፋ መብል አትስሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ህይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ስሩ፡፡እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና፡፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ስራ እንድንሰራ ምን እናድርግ አሉት'' ኢየሱስም መልሶ ይህ የእግዚአብሔር ስራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው፡፡'' ቁ.27-29፡፡ ቁልፍ ነገሩ እዚህ ጋር ነው ያለው ፡፡ ምዕራፉ የሚተነትነው ስለሚበላ የስጋ ምግብ ሳይሆን በክርስቶስ ስለማመን ነው ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ያሉትን ጠቅላላ ቁጥሮች ብንመለከት ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱን በማመን ስለሚገኝ የዘላለም ህይወት እርሱም የህይወት እንጀራ በመሆኑ '' የህይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም፡፡'' ቁ.35

  በእርግጥ ስጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ በሚለው ትምህርቱ ደቀ መዛሙርቶቹ እንኩዋ ሰምተው እንደተሰናከሉ እናነባለን ፡፡ የጌታ መልስ ግን '' ህይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው እንጂ ስጋ ምንም አይጠቅምም ፤እኔ የነገርኩአችሁ ቃል መንፈስ ነው ህይወትም ነው፡፡'' ቁ.63፡፡ ስለዚህ ቃሉ በአጠቃላይ ስጋዎ ደሙን ወይም የጌታ እራት የሚባለውን ስርዓት ለማስረዳትና ትዕዛዝ ለመስጠት የተጻፈ አይደለም፡፡ እርሱን የተነናገረበት ሌሎች ክፍሎች አሉ፡፡ ክፍሎቹ በሙሉ የሚያስረዱት የጌታ እራትን በመውሰድ ስለሚገኝ ጽድቅ ሳይሆን ፡ ድነት ያገኘንበትን ሞቱን እንድናስብ ነው፡፡ ለነገሩ ከስቅለቱና ከሞቱ በፊት የጌታን እራት በመውሰድ እንድንጸድቅ አስቦ ቢሆን፡ ለምን ያን ሁሉ ዋጋ ይከፍላል?፡፡ የመስቀል ላይ ጣሩ፣ የደሙ መፍሰስና ሞቱ በእርሱ አምነን እንድንድን የግድ አስፈላጊ ና ለሐጢያታችን ክፍያ መሆን ስለነበረበት የተደረገ ነው፡፡ ስለ ጽድቅም እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር አልተጻፈም፡፡ የጽድቅ መንገድ እርሱ እንዳለው '' እኔ መንገድ፣ እውነትና ህይወት ነኝ፡ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም '' ዮሐ.14፤6 ፡፡ ብሎአል፡፡ የጽድቅ ብቸኛ መንገድ ክርስቶስ ነው፡፡

    የጌታ እራት ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው?

 

  • የጌታን ሞትና ትንሳኤ መናገሪያ/ማወጂያ/

  •  የቅዱሳን ህብረት ማድረጊያ፡፡ ይህም በአንድነት በምንወስደው ማዕድ በክርስቶስ የተሰጠንን ክርስቲያናዊ ህብረት የበለጠ እናጠናክራለን፤እርስ በርስም እንተናነጻለን፡፡/1ቆሮ.10፡16-18

  •  የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ህብረት ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ከቅዱሳን የእርስ በርስ ግንኙነት በተጨማሪ ከጌታችንም ጋር ህብረት እናደርጋለን፡፡ ቁ.21

የጌታን እራት ማን ሊወስድ ይገባል?

  • የጌታን እራት በክርስቶስ ያመኑ አማኞች ሁሉ ሊወስዱት ይችላሉ፡፡

  •  አንዳንድ ቦታ እንደየ አካባቢውና ህብረተሰቡ ተጨባጭ ሁኔታ ቤተክርስቲያን በአወሳሰድ ጉዳይ የራሱዋን ድንጋጌ ልታወጣ ትችላለች፡፡ ይህም ስርዓቱ መንፈሳዊ ትርጉሙን እንዳያጣ እና እንደ ቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ሁኔታ እንዳይፈጠር በማሰብ ነው፡፡ 1ቆሮ.11፤17-31

  •  በሐጢያት ለመቀጠል ያልወሰነ አማኝ ሁሉ ራሱን መርምሮ መውሰድ ይችላል፡፡

   በእርግጥ ብዙ ጊዜ  ከጌታ ይልቅ፡ ለጌታ እራት የመጠንቀቅ ልማድ ብዙ ምዕመናን ላይ ይስተዋላል፡፡ ይህ ማለት ልባችን ውስጥ ያለውን ክርስቶስን በመፍራት ንስሐ ልንገባ፣ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ልንል ወይም ይቅርታ ልንሰጥ ይገባል እንጂ የጌታ እራት በመጣ ቁጥር ብቻ የምንቀደስና የምንሩዋሩዋጥ ከሆነ፡ ድንገት የሚሆነው ምጻቱ ጊዜ ምን ሊውጠን ነው? ከዚህ በተጨማሪ ድል እና ድነትን ያገኘንበትን የሞቱን መታሰቢያ፡ የሙታን ተስካር እንደሚዘከር ያለ ስርዓት ማካሔድም ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሞቱ ነው ሰይጣን ድል የተደረገው ፣ ሞትና መውጊያው የተሸነፉት፡፡ ሞቱ  ፣ የደረሰበት መከራና እንግልት ሁሉ ቢያሳዝነንም ግን ደግሞ በትንሳኤ የተነሳ ጌታ ነው፡፡ በዕለቱ  የንስሐ መንፈስ ያስፈልጋል ፡ደግሞ ደስ ሊለንና ልንዘምርም ይገባል፡፡

ትርጉሙ ሳይገባን መውሰድ የሚያስከትለው ቅጣት:-

  •  ሳይገባው የጌታን እራት የሚወስድ የጌታ ስጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል፡፡1ቆሮ.11:27

  • ፍርድን ያመጣል፡፡ ቁ.29

  •  ቆሮንቶሶች በጊዜው እንደ ደረሰባቸው አይነት ህመምና ሞት ጭምር ሊከሰት ይችላል፡፡ 1ቆሮ.11፡30

ስለሆነም ወደ ከበረው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራት ከመቅረብዎ በፊት ሁለት ወሳኝ ነገሮን መወሰንዎን አይዘንጉ ፡-

1-እውነተኛ ንስሐ መግባትዎትን

2-ስለ ዓለም ሁሉ ተሰቅሎ የሞተውን ደግሞ በሶስተኛው ቀን የተነሳውን መድኀኒዓለም ክርስቶስን ማመንዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ይህ ሲሆን አይደለም ለጌታ እራት ፡ለመንግሰተ ሰማይም እንኩዋ አይሰጉም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነገር ሁሉ ያግዘን ፡፡ አሜን!

kurban

 የጻድቃን አማላጅነት

 

ክርስቶስ ፈራጅ ነው /አማላጅ  ?

የጻድቃን አማላጀነት ያስፈልጋል ወይ ?

የመላዕክት ድርሻስ ምንድን ነው ? የሚሉትን ነገሮች በስፋት እንዳስሳለን፡፡

በቅድሚያ ጻድቅ የሚባለው ማን ነው?  ምን ያደረገ ነው?  የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተን እንመልስ፡ ጻድቅ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነ ፣ተቀባይነትን ያገኘ ማለት ሲሆን፡፡ ህግጋትን በመፈጸምና አንድም ሀጢያት ባለመፈጸም የታወቀው ብቸኛ ሰው የሆነው ደግሞ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ሁሉ በደልን እንደሰሩ ቃሉ እንዲህ ይላል፡ ‹‹ልዩነት የለምና ሰዎች ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል በክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ  ››  ሮሜ.3፤20-23 ይላል፡፡ 'ልዩነት የለም'  የሚለው ቃል ጻድቅ  እንደሌለ እና በራሱ ተቀባይነትን በእግዚአብሔር ፊት ያገኘ አንድም እንደሌለ ነው የሚያሳየው፡፡ ስለሆነም በክርስቶስ በኩል በእምነት የሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ወደ ሰዎች መጣ  /ሮሜ.5፤1/፡፡

       ‹‹እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ
         ሰው ሁሉ እንደ መጣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ
         ምክንያት ስጦታው ህይወትን ለማጽደቅ  ወደ ሰው
         ሁሉ መጣ፡፡በአንዱ ሰው አለመታዘዝ  ብዙዎች ኀጢያተኞች
         እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች
         ጻድቃን ይሆናሉ፡፡›› ሮሜ.5፡18 ና 19

እግዚአብሔር ያዘጋጀው ጽድቅ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው፡፡ እንጂ ህግን በመፈጸም ና በጎ ተግባራትን በመከወን  አይደለም /ሮሜ.3፡28/፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ጻድቅ ማለት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ  አምኖ የዳነ፣ በደሙም ኀጢያቱን የታጠበ እና በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በጽድቅ እየኖረ ያለ ሰው ነው፡፡

ክርስቶስ ለተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል አይደለም የሞተው ::ለዓለም ሁሉ እንጂ፡፡ስለዚህም ነው መድኀኒዓለም ብለን የምንጠራው፡፡የእርሱ ስቅለትና ሞቱ እኛን ለማዳን በቂ ነው፡፡ለኀጢያታችን የከፈለው ዋጋ፣የፈሰሰው ደም፣የተሰቃየው ስቃይ የሁላችንን እርግማን ለመሻር ና ዕዳችንን ለመክፈል በቂ፣ ከበቂም በላይ ነው፡፡አባቱ በቂ አይደለም! ብሎት በነበረ ኖሮ ሌሎች ተጨማሪ የመዳን ስራዎችን በሰራን ነበር፡፡ነገር ግን እኛን ለማዳን ያነሰ ና የቀረ ነገር አልነበረም የመስቀሉ ስራ አብን አርክቶታል፡፡ ተፈጸመ ብሎኣል፡፡ ስለዚህ ጽድቅ  የማግኛው መንገድ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ ምዕራፍ 14 ቁጥር 6  እንዲ ይላል፡-" እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፡፡በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡"  'በእኔ በቀር'  የሚለው ከጌታችን ኢየሱስ  በስተቀር ማንም ማዳን እንደማይችል ያሳያል፡፡

አማላጅነት የሚለው ቃልና ሀሳብ ብዙ የተሳሳቱ ትርጉም ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ማማለድ ማለት ማስታረቅ፣ማስማማት ማለት ነው:: ይህን ነገር በሁለት ሊስማሙ በሚገባቸው መሀል ገብቶ የሚፈጽመው ሰው አማላጅ /አስታራቂ / ይባላል፡፡ለምሳሌ በዚህ ዘመን እንደሚታወቀው አንድ አገር ከሌላ አገር ጋር ሲጣሉ ሊሸመግሉ የሚገቡት ከተጣሉት አገራት በብዙ ነገራቸው የሚበልጡና ከፍ ያሉ አገራት ናቸው፡፡ለምሳሌ ሁለቱ ሱዳን አገራትን እያስማሙ ያሉት አገራት ፕሬዝዳቶችን ብናይ በፍጹም ከተጣሉት ያነሱ አይደሉም እንደውም ብዙ ጊዜ ከበድ ያለ ሰው ሲመጣ ሽምግልናው ይሳካል፡፡በቤተሰብ ደረጃም ብንሔድ ልጅ ከአባቱ ወይም ከእናቱ ጋር ቢጣላ ወደ ወላጆቹ ለዕረቅ የሚላከው ሰው እናትና አባት ሊሰሙትና ሊያከብሩት የሚችሉት ሰው መሆን አለበት፡፡ይህን ሁሉ የምንለው ማማለድ ማለት የማነስ ምልክት አይደለም ለማለት ነው፡፡

ታዲያ ሰውና እግዚአብሄርንም ለማስታረቅ ከሰውም ሰው የሆነ: ከእግዚአብሔር ጋርም እኩያ የሆነ አስፈላጊ ነበር፡፡ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነ አምላክ በመሆኑ የማማለድን ስራ ሰራ፡፡ እርቁ ግን ከአብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጋር ነበር፡፡

ይማልዳል / ያስታርቃል/ ሲባል ተንበርክኮ ይለምናል ፣ዝቅ ብሎ ይለማመጣል ማለት አይደለም፡፡እንኩዋን እርሱ ከላይ የጠቀስናቸው የአገራት ሽማግሌዎች  ተደፍተው አይለምኑም፡፡ነገር ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ የሆነበት ደሙ በአብ ፊት ዘውትር ይታያል ማለት እንጂ፡፡ስለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ ሲጠቅስ ''እርሱ ግን ስለ ኀጢያት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ  ተቀመጠ፡'' የሚለን፡፡ ዕብ. 10፤12  በተጨማሪ  9፤28ን ያንብቡ፡፡

አሁን በሰማይ እገሌንም ይቅር በለው እገሊትንም ይቅር በላት እያለ የሚለመንበት ዓይነት የምልጃ ስርዐት  ይኖራል ብለን አንጠብቅም፡፡ በክርስቶስ በኩል የቀረቡትን ሁሉ  ከሐጢያትና ከበደል ነጻ የሚያደርግ ቅዱስ  ደም ግን አለ፡፡ ደሙ ስለ ሁላችን ሐጢያት ማስተሰርያ እንዲሆን የፈሰሰ ነው፡፡

ክርስቶስ ስለ እኛ ይማልዳል! የሚለውም ቃል /ሮሜ 8፤34/ ከላይ በተገለጠው አግባብ ካልተፈታ በቀር ሌላ ነገር እንድንረዳ ሊያደርገን ይችላል፡፡አምላክ ሆኖ እንዴት ዝቅ ይላል እንዴት ይማልዳል ? ክርስቶስ ፈራጅ ነው አማላጅ?  የሚሉ ጥያቄዎች/ አሳቦች/ በስፋት  ይነሳሉ ፡፡ለነገሩ አምላክ ሆኖ እንዴት ያማልዳል? ከሚለው ነገር ይልቅ አምላክ ሆኖ እንዴት ይሞታል? የሚለው ነው ከባድ መሆን የነበረበት፡፡ነገር ግን አምላክ የሆነው ኢየሱስ  መከራን ተቀብሎአል፣ ተገርፎአል፣ ተሰቅሎአል፣ ሞቶኣል፡፡የማዳን ስራውም ተፈጽሞአል፡፡ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ማናቸውም ሰዎች በደሙ ነጽተው ይጸድቃሉ፡፡እርሱ በስጋው ወራት የከፈለው የሀጢያት ክፍያና ከብርቱ ጩኸት ጋር ያቀረበው ምልጃ፣ አጠቃላይ የመስቀል ስራው ህያው ሆኖ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ ይታይላቸዋል፡፡ክፍያው ስለ ሰው ልጅ ሁሉ  ነውና፡፡

 

የጻድቃን ምልጃ

 

ጻድቃን በምድር ሳሉ በምድር ላይ ገና በህይወት ላሉት ሰዎች ሊጸልዩ ና ሊያማልዱ ይችላሉ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያምም አማልዳለች፡፡የሰዎችን ጉዳይ ለልጁዋ ነግራለች ከዚህም በላይ ከበጉ ሐዋርያት ጋር አብራ ጸልያለች፡፡ምናልባት ወንጌል ገና ስላልደረሰበት የአለም ክፍሎች አሳስበው ይሆን?  ሌላም ብዙ የሰዎችን የተወሳሰበ ጉዳየ ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ቀርበው ይሆናል፡፡ምን እንደ ጸለዩ ነው እንጂ የማናውቀው መጸለያቸውን እናውቃለን፡፡ሐዋ. ስራ 1፤14፡፡

አለምን ሁሉ ከአብ ጋር የማስታረቅና የማዳን ስራ ግን የተሰራው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ በመሆኑ፤ ጻድቃንም ሆኑ ሰማዕታት ሰዎችን የማዳንም ሆነ መንግስተ ሰማይ የማስገባት ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ የዘላለም ህይወት ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነገር ቢሆንማ ኖሮ  ክርስቶስ መጥቶ ባልተሰቀለ፤ያን ሁሉ ዋጋ ባልከፈለ ነበር፡፡ እርሱ በስጋ ሳይወለድ እኮ ነብያት፣ አባቶች፣ ነበሩ፡፡ግን መዳን በእነርሱ በኩል ሊፈጸም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ነው የጌታችን መምጣት የግድ የሆነው፡፡

ከመዳን ጉዳይ ባሻገር ለተለያዩ ጉዳዮችም ቢሆን የሞቱ ቅዱሳን በህይወት ስላሉት ሊለምኑና የሰዎችን ጸሎት ሁሉ ሊሰሙ  እንዴት ይችላሉ? በመጀመሪያ ከፈጣሪ በስተቀር ሁሉ ፍጡራን  ናቸው፡፡ምድራዊ እናትና አባት ኖሮአቸው የተወለዱ በጊዜና በስፍራ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው መሞታቸው፡፡ ከላይ ሆነው ሁሉን ማየት እንደ እግዚአብሔር ከቻሉ እኮ: መለኮት ሆነዋል ማለት ነው ፤ግን እንደዛ አይደለም፡፡

 

              መላዕክት

 

በዚሀም ላይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ እልፍ አዕላፋት የሆኑት፤ አንድ መልዐክ ሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘት ስለማይችልና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መስማት ስለማይችል ነው፡፡ለምሳሌ አብሳሪውን የጌታ ታማኝ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤልን እንውሰድ ዕለተ ቀኑ በሚባለው 19 ምናልባት ታህሳስ 19  ንግስ ተብሎ በሚነገረው ቀን ፤ካሉት በርካታ በስሙ የተሰየሙ አብያተክርስቲያናት መካከል መርጦ የሚገኘው የትኛው ክልል ነው? የትኛውስ ቤተክርስቲያን ነው? ምክንያቱም አንድ ነው ብለናል፡፡ ሁሉን መቻል / Omnipotent /፣ ሁሉን ማወቅ / Omniscience  /፣ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት / Omnipresent    / የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ባህሪ ነው፡፡ሁሉም ጻድቃን፤ መላዕክት ሁሉን ማወቅ፤በሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘትና የሁሉን ሰው ጸሎት ማድመጥ የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር የሚባለው አምላክ ምን ልዩነት አለው ታዲያ?  ነገር ግን እውነቱ እነዚህ ባህርያት ማንንም ያላጋራበት የስላሴ ብቻ የሆነ ነው፡፡ ስላሴን የተለየ የሚያደርጋቸውም ይህ ባህሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የኢየሱስን እናት ማርያምን ሊያበስራት የመጣ ጊዜ እርሱን ሌላ ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በዚያ ጊዜ አጣዳፊ ጉዳይ ካለ እንኩዋ ሌላ መልአክ ነው የሚላከው:: ምክንያቱም አንድ መልዐክ መገኘት የሚችለው በአንድ ቦታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ወደ ዳንኤል መልስ ይዞ  እየበረረ ይመጣ የነበረውን መልዐክ  /አንዳንድ ሰዎች ገብርኤል  እንደሆነ ይላሉ/  የፋርስ አለቃ  (የፋርስ መንግስት አገር  ላይ በአየሩ ላይ አለቃ የነበረ አጋንንት) እንዳያልፍ ከልክሎት እንደነበር፤ ለ 21 ቀናትም ተቸግሮ እንደነበር ማወቁ ጥሩ ነው፡፡በሁዋላም ወደ ዳንኤል መምጣት የቻለው የመላዕከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ስለመጣ ነበር /ዳን.10፤13-20/፡፡ መላዕክት ሲላኩ በቦታ በስፍራ የሚወሰኑ መሆናቸውን ተመለከታችሁ? እንዳይመጣ ተከልክሎስ እንደ ነበረ አያችሁ?

መላዕክቶችም ሆኑ ቅዱሳን ወደ ጠሩአቸው ሁሉ የመሄድ፣ እንደወደዱ የማድረግ ማንነት አይደለም ያላቸው፡፡ መላዕክትነታቸው ለእግዚአብሔር ነውና እርሱ ወደ ላካቸው ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ እርሱ ያዘዛቸውንም ይፈጽማሉ፡፡ ይህን እውነት ማወቅና መናገር እነርሱን ማዋረድ ማለት አይደለም፡፡ በፍጹም እነርሱን ዝቅ ማድረግም አይደለም፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡አብርሐም ቤት የመጡት መላዕክት አብርሀም ቤት ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነው  ሎጥ ዘንድ ሰዶም የሄዱት፡፡

 

ከመጀመሪያው ግን ከዘላለም  ሞት እንዲያድኑንና እንዲያስታርቁን ተሹመው በነበረ ፡አለመታዘዛችን ነበር ሀጢያት የሚሆን፡፡እነርሱም ብዙ በታዘቡን ነበር፡፡ አሁን ግን ከገረማቸው እንኩዋ  ሊገርማቸው  የሚችለው እነርሱ  ለእረኞች ያበሰሩትን ጉዳይ ያለመታዘዛችንን ሲያዩ ነው  /ሉቃ.2፤9-14/፡፡ የፃድቃንም አግራሞት ለእነርሱም መደሀኒት ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አለማተኮራችን ነው፡፡ ቅድስት  ማርያምም ከገረማት እንኩዋ የሚገርማት ‹አርሱን ሰሙት›  ያለችውን፣ መድሀኒቴ አምላኬ ባለችው ልጁዋ አለማመናችን ነው፡፡ስለ ሁሉም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በመስቀል ላይ ስለ ከፈልክልኝ ዋጋ አመሰግንሀለሁ፡፡በቀራንዮ መስቀል በፈሰሰው ደምህ ሀጢያቴን እጠብልኝ ከበደሌም አንጻኝ፤ወደ ልቤም ገብተህ አብረኸኝ ኑር በማለት ከልባችን  ንስሀ  እየገባን በመጸለይ   ራሳችንን ለመንግስተ ሰማይ እናዘጋጅ፡፡የጌታችን ዳግም ምፅዐት ቀን ተቃርቡዋል፡፡ ከእግዚአብሔር በኩል ያለው ነገር ሁሉ ተሰርቶ አልቁዋል፤ ከእኛ በኩል የቀረውን እናድርግ!! ሰምተን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡

Milja

 

የሙታን ተስካርና ዝክር

  

በዚህ በክፍል ሁለት ትምህርት ውስጥ ካለፈው የቀጠለውንና ከዚህ ሐሳብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች እናነሳለን፡፡

  • ሐጢያትን  ለካህን  መናዘዝ  ተገቢ  ነውን ?

  • የአዲስ ኪዳን  ዘመን  ካህናት  እና ሊቀ  ካህን  ማን ነው?

  •  በጻድቃን  ስም  ቀዝቃዛ  ውሀ  ማጠጣት  ያጸድቃል?

  •  ዝክር  መዘከርና  ምጽዋት  ማድረግ  ለጽድቅ  ይጠቅማል?

  • የሙታን  ተስካር  ወይም  /ፑርጋቶሪ/ ምንድን  ነው?

 

                  የአዲስ ኪዳን  ካህናት እነማን ናቸው?

        ስለ ካህናት ስናነሳ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፡ ካህናት በብሉይ ኪዳን የነበራቸው ሚና እና የአዲስ ኪዳን ክህነት ምን እንደሆነ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት የሚመረጡት ከሌዊ ነገድ ሲሆን ምግባራቸውም የቤተ መቅደሱን መንፈሳዊ ስርዐት መምራት ነው፡፡ በተለይም ለኀጢያት ስርየት የሚቀርቡ መባ ና መስዋዕቶችን ህዝቡን ወክለው በእግዚአብሄር ፊት የሚያቀርቡት እነርሱ ነበሩ፡፡ የብሉይ ኪዳን ህዝብ ሐጢያቱን የሚናዘዘው የሚሰዋው በግ ወይም ጠቦት ላይ ሲሆን ሊቀ ካህኑም ደሙን ይዞ በአመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፡፡/ ዕብ.9፤6-7 /

  በአዲስ ኪዳን ዘመን ለሐጢያት ተብሎ የሚቀርብ መስዋዕት ወይም ደም የለም፡፡ሊቀ ካህናችን የሆነው ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ ደሙን ይዞ ወደ እውነተኛው የሰማይ መቅደስ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡/ዕብ.10፤11-18/ በአሁኑ ሰዐት እስራኤላውያን፣ ካህናቱ ሌዋውያንን ጨምሮ በተወሰነ መንገድ ስርዐቱን የሚከተሉ ቢሆንም የእውነተኛውን አዳኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ና ጌትነት ግን አልተቀበሉም፡፡

 

               የማሰርና የመፍታት ስልጣን...!

        የማሰርና የመፍታት ስልጣን የተሰጣቸው ካህናት እነማን ናቸው? በማቴዎስ ወንጌል ም.18 ቁ.18 ላይ እንደተጠቀሰው "...እውነት እላችሁዋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡":: በሌላም ስፍራ  ጌታ ለጴጥሮስ እንደተናገረው " የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሀለሁ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ማቴ.16፤18፡፡ አንባቢ  እንደሚረዳው እነዚህ ቃላት የተነገሩት የመጀመሪያው ጥቅስ የጌታችን ደቀመዛሙርት ለነበሩት ለመጀመሪያዎቹ የበጉ ሐዋርያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለሊቀ ሐዋርያው ለጴጥሮስ የተነገረ ነው፡፡መሰረታዊውን ታሪክ ለማስታወስ ብዬ ነው እንጂ፤ በሌላ ዘመን ለሌሎች ክርስቲያኖች ቃሉ አይሰራም ለማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ሰዎች ናቸው፤ በክርሰቶስ በመሲሁ አዳኝነት ያመኑ እስራኤላውያን ናቸው፤ ደግሞ የክርስቶስ ሞቱና ትንሳኤው ምስክር ለመሆን የተመረጡ ወንጌል ሰባኪዎች  ናቸው፡፡ ለእነርሱ ግን የተለየ ልብስ እና የተለየ ጥምጥም አልነበራቸውም፡፡

     ሁለቱም ሐሳብ የብሉይ ኪዳንን ስርዐት ስለሚከተሉ ካህናት አይናገርም፡፡ ለእነርሱ እንዲህ ያለ ስልጣን የላቸውም፡፡ እንደዚህ ለመሆን አስቀድሞ በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነበረባቸው፡፡

     ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ያንን ለምጻም ከፈወሰ በሁዋላ " ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ !" ሉቃ.5፤14 ያለውስ ጉዳይ ? ብለን ብናነሳ፡ በቅድሚያ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣበት ጊዜ በምድር ላይ የነበረው ስርዐት የአይሁድ ስርዐት እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ፈጽሞ አዲስ ኪዳንን እስኪተካ ድረስ የሙሴን  ህግ በመታዘዝ ነው ይህንን ያደረገው፡፡ አንደኛ ህግን ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ነው የመጣሁት ስላለ ማቴ. 5፤17፡፡ ሁለተኛው በዘመኑ የነበሩ ፈሪሳውያን ሙሴን ህግ ይሽራል የሚል ተደጋጋሚ ክስ ቢያነሱም፡ እርሱ ግን ያንን አለማድረጉን ካሳየበት አንዱ ማሳያ ይህ ታሪክ ነው፡፡በሙሴ ህግ እንደተቀመጠው ሰው በለምጹ ከሰፈር ከተወገደ በሁዋላ ሌላ ጊዜ በሆነው መንገድ ቢፈወስ ወደ ህብረተሰቡ ከመቀላቀሉ በፊት ራሱን ለዘመኑ ካህናት ማሳየት ነበረበት፡፡ካህኑም መንጻቱን አረጋግጦ ወደ ሰፈር ይቀላቅለው ነበር፡ ዘሌዋውያን 14፤2-32፡፡ ስለዚህም ጌታ የፈወሰውን ያንን ለምጻም በህጉ መሰረት በካህናቱ እንዲታይ ነው የሰደደው፡፡ ያንንም ያደረገው በትህትናና በታዛዥነቱ ነው፡፡ በዚህም ላይ የነጻን ለምጽ ሄዶ ለካህናት ማስፈተሸ ሐጢያትን ለእነርሱ ከመናዘዝ ጋር ምን ግንኙነት አለው? በዘመኑ የብሉይ ኪዳን ካህናት ከለምጹ የነጻን ሰው የሚፈትሹት እነርሱ ነበሩና ያንን አደረገ፡፡ከህጉ በላይ የሚቀኑለትን ወግና ስርዐታቸውን ግን አጥብቆ ይኮነንን ነበር፡ /ማር.7፤14-21/

     የአዲስ ኪዳን ዘመን ህዝብ ሐጢያቱን መናዘዝ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኩል  በቀጥታ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህንና መካከለኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ዕብ.9፤15፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ካህናት ተብለው ተጠርተዋል፡፡!1ጴጥ.2፡9 ፡፡በዚ መሰረት አንዱ ስለ አንዱ እርስ በእርስ ሊጸልይ ይችላል እንጂ፤ ለብቻው የተለየ ልብስ የለበሰ እና ለእርሱ ብቻ የሚገባ የጸሎት መጽሐፍ እያነበበ ንስሐ የሚያድል እና የህዝብን ሐጢያት የሚያስተሰርይ ሰዋዊ የክህነት ስርዐት የለም፡፡እግዚአብሔር  ሁሉንም ሰው በአንድ ጊዜ መስማት ስለሚችል፤ በፊቱ ንስሀ የሚገቡትን ሁሉ በክርስቶስ ይቅር ይላቸዋል፡፡ 1ዮሐ.1፡4-9፣ሥራ.10፤48፡፡

 

             በጻድቅ ስም  ውሀ  የሚያጠጣ .. !?

" እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይወስዳል፡፡ማንም  ከእነዚህ  ከታናናሾቹ ለአንዱ  ቀዝቃዛ  ጽዋ ውሀ  ብቻ  በደቀ መዝሙሩ ስም የሚያጠጣ አውነት እላችሁአለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ " ማቴ.10፤40-42፡፡

 በጥሞና አንድ ጥያቄ እናንሳ የነቢያትና የጻድቃን ዋጋቸው ምንድን ነው?  ነቢይ እግዚአብሄርን ሰምቶ ላመጣው መልዕክት፡ ዋጋው ሰው ሲመለስ ፣ንስሀ ሲገባ ማየት ፣ከመቅሰፍት ከዕልቂት አምልጦ በፈንታው ለእግዚአብሔር እየተገዛ ሲኖር ማየት ነው፡፡ ጻድቅም አመጻን ጠልቶ  በጽድቅ ለኖረበት ኑሮ ጌታ የሚከፍለው መንፈሳዊና ስጋዊ በረከት ነው፡፡ ስለ መንግስተ ሰማይ ስለ መግባት ጉዳይማ ቢሆን ማንም ቢሆን በህግ እና በስራ አይድንም /ኤፌ.2፤8-9/፡፡ ከዚህ ጋር ሌላው ዋና ነገር  " እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል " የሚለው ቃል ነው፡፡ ጻድቃንን ስንቀበል የምንቀበለው እነርሱ የሚሰብኩትን መድሐኒታችንን ኢየሱስን ነው፡፡ እርሱ እነርሱን ያዳነና ያጸደቀ በመሆኑ ልክ እነርሱን ተቀብለን ስናስተናግድ፣ ስንሰማቸው ፡ስበኩ ብሎ የላካቸውን ጌታ እንቀበላለን፡፡ ጻድቃንን የተቀበላችሁ ወገኖቼ  መስክሩ ብሎ የላካቸውን ኢየሱስንስ ተቀብላችሁዋል?? እርሱ እናንተን  የሚቀበል እኔን ይቀበላል ብሎአልና፡፡  በደቀ መዝሙሩ ስም ቀዝቃዛ ውሀ  የሚያጠጡ ሰዎችም ዋጋቸው አይጠፋም! ነው  እንጂ  የሚለው  አጸድቃቸዋለሁ አይደለም፡፡ ዋጋው /ክፍያው/ ብዙ ዓይነት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ለዘላለም ህይወት መንገዱ ግን አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሰው በሆነው በክርስቶስ አምኖ ንስሐ መግባት ነው፡፡/ዮሐ.14፤6/፡፡

  አያይዘን ዝክርን፣ ምጽዋትን፣ ሌሎች ለጽድቅ ተብለው የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ ብንመለከት እንዴት መንግስተ ሰማይ ለመግባት ሊጠቅሙን ይችላሉ?  በእንደዚህ ሁኔታ መዳን ቢቻል ኖሮ ለምን መድኀኒዓለም መጥቶ ዋጋ  ከፈለልን ? ለምን ተገረፈ ?፣ ተሰቀለ ?፣ ሞተ ?፣ ተቀበረ ? ለምን ?? ቃሉ የሚለን  " ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ስራ እንዳይሆን ስጋን የለበሰ ሁሉ በህግ ስራ ስለ ማይጸድቅ እኛ ራሳችን...እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፡፡ ገላ.2፤16፡፡ በሐዋርያት ሥራ 4 ቁ.12 ላይ እንደተገለጠውም ወአልቦ፡ ካልእ፡ ሕይወት፡ ወአልቦ፡ ካልእ፡ ስም፡ በታሕተ፡ ሰማይ፡ ዘይትወሀብ፡ ለእጉዋለ፡ እመሕያው፡ በዘ፡ የሐዩ፡፡ /መዳን በሌላ በማንም የለም፡እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ  ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡"

   ቆርነሌዎስ የሚባለው ሰው / በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 10፤1-48 ላይ የምናገኘው/ ፡ ለጽድቅ ብሎ ብዙ ነገሮችን ይፈጽም ነበር፤ ለምሳሌ ይጾም ነበር፣ ከቤተሰዎቹ ጋር እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክ ነበር፣ ለድሆች እጅግ ምጽዋት ያደርግ  ነበር፡፡ ምንም እንኩዋ ድርጊቱ ደስ የሚያሰኝና እግዚአብሔር ዘንድ የደረሰም ቢሆን ለመጽደቅ ግን ዋነኞች ጉዳይ ስላልነበሩ፡ መልዐክ  ወደ እርሱ ዘንድ ተልኮ ስለ ክርስቶስ ወንጌል የሚነግረው፣ እንዲያምን የሚረዳውና የሚያስተምረው ደቀመዝሙር ጠቁሞት ልኮ አስመጥቶታል፡፡ ያደረገው ነገር ሁሉ ለመዳኑ በቂ  ከነበረ  ጴጥሮስ ለምን ወንጌል እንዲነግረው ታዘዘ ?  መልካም ስራዎች ሁሉ በጌታ ያመኑና የጸደቁ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመልካም ስራቸው ጌታቸውን ማስመሰገንና መግለጥ ስላለባቸው፡፡ በጎ ስራ መስራት ዝክር፣ ጾምና ጸሎት፣ ምጽዋት ማድረግ ግን ብቻውን አያጸድቅም፡፡

              የሙታን ተስካር

  ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ይገባል! የሚሉ ሰዎች መነሻ ጥቅሳቸው 2ኛ መቃቢያን 12፡41-46 / ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባለ አዋልድ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ/ ሲሆን፤ በእርገግጥ በጥንት ጊዜ ጀምሮ በቻይናውያን እምነትም ዘንድ እንደ ቡዲዝም ባሉት እምነቶች ሙታንን ወክለው መስዋዕት ማቅረብ የተለመደ ነገር ነው፡፡

 ለሙታን መጸለይ /ፑርጋቶሪ/ አንድ ሰው ከሞተ በሁዋላ ነፍሱ ሲኦል ትገባለች፤ ነገር ግን ቤተሰቦቹና ዘመድ አዝማድ ከሞተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በየተወሰነው ጊዜ በስሙ ዝክር ቢያወጡለት ቀስ በቀስ ከሲኦል እየወጣ ይመጣና በሂደት ገነት ይገባል የሚል የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የምናነሳቸው የገድላት መጽሐፍት ለዚህ ትምህርት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

  1.   ነገር ግን ሉቃስ 16 ቁ.19-31 ከቀረበውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው ምሳሌ እውነቱን  መማር እንችላለን፡ አንድ ሰው የሆነውን ሆኖ ከሞተ ወዲያ ሰማይ ላይ ሔዶ የሚያስቀይረው ሐሳብ የለም፡፡ በጻድቃን ሰማዕታት ምልጃና ልመናም መዳን አይችልም፡፡ ክፍሉ ላይ እንደተመለከተው ሐብታሙ ሰው ከሲኦል ሆኖ ምንም አብርሐምን በእሳት እየተንገበገበ ቢለምንም '' በዚህ ያሉ ማለትም በአብርሐም እቅፍ ውስጥ በእረፍት ያሉ ወደ ስቃዩ ስፍራ መሄድና ማዳን እንዳይችሉ በመካከል ታላቅ ገደብ ተደርጎአል:: '' ነው ያለው፡፡ / በገነት ያሉ ወደ ሲኦል ፤በሲኦል ያሉ ወደ ገነት መምጣት አይችሉም ! / ፡፡ ከዚያ በሁኣላ በምድር ላይ አባቱ  ቤት ስላሉ 5ት ወንድሞቹ  ነው የተጨነቀው፡፡ ወደዚህ ስቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ሰው ከሞት ተነስቶ ይመስክርላቸው ብሎ ተማጸነ፡፡ ምናልባት እንደርሱ ሰማይ ስንሔድ ጻድቃን ሰማዕታት አሉልን! ብለው ተዘናግተው ከሆነ እንኩዋ፤እውነቱ ያ እንዳልሆነ ስለተረዳ ይሆን ?  ለማንኛውም ለዚህም ጥያቄ ቢሆን እዛው ምድር ላይ ያሉትን መስካሪዎች /ሙሴና ኤልያስ አሉላቸው / እነርሱን  ይስሙ ነው የተባለው፡፡ ተመለከታችሁ በሰማይ ምንም አይነት ቀልድ እንደሌለ? ሐጢያተኛ ሰው ከሞተ ወዲያ፡ ፍርድ ብቻ ነው የሚጠብቀው፤ አንድ  ጊዜ  በፍርድ  ሲኦል  የገባን   ነፍስ  ተከራክሮ ፣ ውሳኔ  አስቀይሮ  ወደ ገነት ሊያመጣ  የሚችል  አንድም  መልዐክ  ወይም  ጻድቅ  የለም!!!   ወገኖቼ አንሞኝ ዛሬውኑ ፡ቀን ሳለልን ፣ትንፋሻችን ሳይቆም በክርስቶስ አምነን እንዳን ! አውነተኛ ንስሐም እንግባ፡፡ ጌታ ሆይ ሐጢያቴን ይቅር በለኝ ልጅህን ኢየሱስን የህይወቴ አዳኝ አድርጌ እቀበላለሁ እንበል፡፡ አሁኑኑ ባሉበት ቦታ ሆነው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

Teskar

© 2016 by AL Consulting LLC. Proudly created with Wix.com

  • Twitter Classic
  • c-facebook
bottom of page